የጉራጌ ዞን የ2014 የልዩ ልዩ ስፖርታዊ ሻምፒዮና እና የባህል ስፖርት ውድድሮች በዛሬው እለት ፍጻሜ አግኝተዋል ።በውድድሩ የተሻለ እንቅስቃሴ የነበራቸው ተጫዋቾች በወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ እንዲታቀፉ እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገለፀ።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል የ2014 የልዩ ልዩ ስፖርታዊ ሻምፒዮና እና የባህል ስፖርት ውድድሮች መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር ስፖርት ሁሌም የሚሰራ እንጂ ተሰባስበን በመበተን የምናሸንፈው እና ተሸንፈን ቤት የምንገባበት ውድድር አይደለም ብለዋል።ዛሬ የተሸነፈ ነገ የሚያሸንፍ በመሆኑ ሁሌም በስፖርት የሚያሳልፉና በእዚህ የውድድር ሜዳ በመገኘት አቅማቸውን ላሳዩ መምህራን ፣ ብዙዎች ዋጋ ከፍለው የዋንጫ ባለቤት ለሆኑና በውድድሩ ድል ላልቀናቸው አሰልጣኞችና ተጫዋቾች ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል አቶ መሀመድ ።በተደረጉ ውድድሮች ዞኑን ወክለው የተመረጡ ተጫዋቾች የዞኑ አምባሳደሮች በመሆናቸው የዞኑን ባህልና እሴት ተላብሰው በቀጣይ በክልሉ በሚካሄዱ ውድድሮች አመርቂ ውጤት ማምጣት እንደሚጠበቅባቸው ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።አያይዘውም አቶ መሐመድ ታዳጊዎች በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ለማብቃት ዞናዊ ውድድር ከማዘጋጀት በተጨማሪ በውድድሩ የተሻለ እንቅስቃሴ የነበራቸው ተጫዋቾች በወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ እንዲታቀፉ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አወል ጅማቶ በበኩላቸው የስፖርቱ ቤተሰቦች በውድድሩ ያሳዩት ስፖርታዊ ጨዋነት ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስችሎታል ብለዋል።በተወዳዳሪዎቹ መካከል የነበረው ጠንካራ ፉክክር ተተኪ ስፖርተኞች ለመለየት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የተናገሩት ኃላፊው በቀጣይ በደቡብ ክልል የልዩ ልዩ ስፖርታዊ ሻምፒዮና የሚሳተፉ ስፖርተኞች ተመልምለዋል ብለዋል።የዞኑ ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ሻምፒዮናው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የስፖርት ማህበራት፣ ዳኞችን፣ የቡታጅራ ከተማ አስተዳደርና የመስቃን ወረዳ አስተዳደር እንዲሁም መላው የስፖርት ቤተሰብ የነበራቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ምስጋና አቅርበዋል። ኢንስትራክተር ቸሩ ጠበል በሰጡት አስተያየት ውድድሩ ፍጹም ሰላማዊ እና ስፖርታዊ ጨዋነት ተላብሶ እንዲጠናቀቅ የዳኞች አበርክቶ ከፍተኛ ነበር ብለዋል።በዞኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዳኞች እንዳሉ የተናገሩት ኢንስትራክተር ቸሩ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ ዳኞች ውድድሮቹ በብቃት መዳኘታቸውን ገልጸዋል።በእግር ኳስ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት የጉንችሬ ከተማ እና የማረቆ ወረዳ ጨዋታ አስከ 90 ደቂቃ ባለው ጊዜ አንድ አቻ አጠናቀው በተሰጣቸው የቅጣት ምት ጉንችሬ ከተማ 3 ለ0 በሆነ ውጤት የማረቆ አቻውን አሸንፎ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል ።በተለያዩ ውድድሮች አሸናፊ የሆኑ ወረዳዎችና ተጫዋቾች የዋንጫና የሜዳልያ ሽልማት አግኝተው ውድድሩ ተጠናቋል። = ኢትዮጵያን እናልማ! = የፈረሰውን እንገንባ! = ለፈተና እንዘጋጅ! በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡ Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone Website:- https://gurage.gov.et Telegram:- https://t.me/comminuca Youtub: –https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *