Public Service & Human Resource

የሴክተሩ አጠቃላይ ገጽታ

የፐብሊክ ሰርቪሱን የማስፈጸም አቅም ለማጎልበት የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም ተቀርጾ የተለያዩ የሪፎርም ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ምክንያቱም መንግስት የሚነድፋቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በማስፈጸም ረገድ ፐብሊክ ሰርቫንቱ ቁልፍ መሳሪያ ከመሆኑም ባሻገር የመንግስትን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የፍትህ አገልግሎት ወደ ዜጎች ማስተላለፊያና ማድረሻ ብቸኛ መንገድ በመሆናቸው ነው፡፡ በነዚህ የማሻሻያ ፕሮግራም ስራዎች አማካይነት በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን የተገኘው ውጤት መንግስትንም ሆነ ዜጎችን በሚፈልጉት ጊዜና የጥራት ደረጃ ተከናውኖ በማርካት ረገድ ሠፊ ክፍተት እንዳለበት ከመታየቱም ባሻገር ፐብሊክ ሰርቫንቱ በአገልጋይነት ስሜት የተሞላ ቀልጣፋ መንግስታዊ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ማቅረብ ያልቻለበትና ለመልካም አስተዳደር ችግር መፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ በመሆኑም ይህንን ስር የሰደደ ችግር ከመሠረቱ ለማስወገድ በጠንካራ መሠረት ላይ የሚቆሙ ዘላቂ የሆነ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅማቸውን በመገንባት እንዲሁም ለሃገራችን ብልጽግናና ለዜጎች እርካታ አስተዋጽኦ የሚያድርጉ ጠንካራ ተቋማት መገንባት ዋነኛ ቁልፍ ሥራ ነው፡፡

ከዚህ መሠረተ-ሀሳብ በመነሳት በዞናችን በየደረጃው የሚገኙትን የመንግስት ተቋማትን የማስፈጸም አቅም ለመገንባትና በዞናችን ብሎም ለሃገራችን ብልጽግና አስተዋጽኡ ሊያደርጉ የሚችሉ ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት ትኩረት ያደረገ የቀጣይ አሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ ዕቅዱ በዋናነት በሴክተር ተኮር ሪፎርም ትግበራና አመራር ላይ የተመሠረተ ሲሆን ያለፉትን የአንደኛና የሁለተኛ የዕድገትና ትራንፎርሜሽን ዕቅዶችን አፈጻጸም ገምግሞ ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንዲሁም የቀጣይ ዕቅድ ዘመን መልካም አጋጣሚዎችንና ሥጋቶችን ለይቷል፡፡ በቀጣይ አስር ዓመታት በሴክተሩ በየደረጃው በሚገኙ ተቋማትና ባለድርሻ አካለት ጋር የሚከናወኑ ጉዳዮችን በአምስት የትኩረት አቅጣጫዎች ይዳስሳል፡፡ እነዚህም የትኩረት አቅጣጫዎች የተቋማትን የማስፈጸም አቅም መገንባት፤ የሰዉ ሀብት ልማትና ስራ አመራር ስርዓት ማሻሻል፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ የመልካም አስተዳደርን ማስፈን እና የሲቪል ሰርቪስ ስነ ምግባርን ማሻሻል ናቸው፡፡ በእነዚህ አምስት የትኩረት አቅጣጫዎች ሥር ስትራቴጂክ ግቦች ከነ ውጤቶቻቸውና ዒላማዎቻቸው ጭምር ተጥለዋል፡፡ ይህንን መሪ ዕቅድ ለማከናወን በቀጣይ አስር ዓመታት የሚያስፈልጉ የመስሪያቤቱ መነሻ አቅሞች ወይም ሰብአዊና ቁሣዊ ሀብት ማለትም የሰው ሀብትን በተመለከተ፣የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች አቅርቦትና አጠቃቀምና ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር መኖር ተተንትኖ ተቀምል፡፡ በተጨማሪም የግቦችን አፈጻጸም ለማሳለጥና ውጤታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ስትራቴጂክ ዕርምጃዎች ከሚያሳኳቸው ግቦች አንጻር ተለይተው የተቀመጡ ሲሆን በመጨረሻም ለአሥር ዓመቱ መሪ ዕቅድ ማስፈጸሚያ የሚውል በጀት ካለፈው አስር አመት አፈጻጸም ጋር በማነጻጸር በሃያ በመቶ ዕድገት በማስላት ማለትም ብር 33‚274‚612.90 (ሰላሳ ሶስት ሚሊየን ሁለት መቶ ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ አስራ ሁለት ብር ከዘጠና ሳንቲም) ተቀምል፡፡

የሴክተሩ ተልዕኮ፣ ራዕይና እሴቶች

ተልዕኮ

በዞኑ የመንግስትን ፖሊሲዎችና ስትራቴጀዎች በብቃት ለመፈጸም የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችንና አደረጃጀቶችን በመዘርጋት፣ የአመራሩንና የሰራተኛዉን አመለካከት በመለወጥና ብቃቱን በማሳደግ፣ ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት የሚያገለግል ጠንካራና ዉጤታማ ሲቪል ሰርቪስ መፍጠር ነዉ፡፡

ራዕይ

ተልዕኮውን በብቃት መፈጸም የሚችል በሥነ-ምግባሩ የተመሰገነ ሲቪል ሰርቪስ ተፈጥሮ ማየት፡፡

እሴቶች

  • ለለውጥ መስራት
  • ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት
  • ቅንነት፣ ታማኝነትና አገልጋይነት
  • ሁሌም መማር
  • ውጤት ያሸልማል
  • በጋራ መስራት
  • አለማዳላት

የተቋሙ የትኩረት መስኮች

የትኩረት መስክ 1፡ የተቋማትን የማስፈጸም አቅም መገንባት

በዚህ የትኩረት መስክ ውስጥ ሦስቱ የማስፈጸም አቅሞች ማለትም የሰው ኃይል፣ አደረጃጀትና አሰራርን ለማሻሻል ትኩረት ይደረግባቸዋል፡፡ በዚሁ መሰረት የሪፎርም ፕሮግራሞችን በማጠናከር እና የተለያዩ የለውጥ መሳሪያዎችን ላይ አመራሩንና ፈፃሚውን የማሰልጠንና የማላመድ፣ የማማከርና ወጥነት ባለው መልኩ እንዲተገበሩ የማድረግ፣ የተጠኑ የተቋማትን አደረጃጀት ማስተግበር በዞኑ መንግስት ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ውጤታማና የህዝብ እርካታና አመኔታ የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ በለውጥ ሰራዊት አሰራርና አደረጃጀት መሠረት የመፈጸም አቅም እንዲጎለብት ይደረጋል፡፡

የትኩረት መስክ 2፡ አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል

የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት መንግስታዊ ተቋማት የተገልጋዮቻቸውን ፍላጎት ለማርካት በተሰጣቸው ተልዕኮ መሰረት የሚፈጽሙት ተግባር ነው፡፡ ይህ አቅጣጫዉ የሚያተኩረዉ በሲቪል ሰርቨሱ የሚሰጡ ልዩ ልዩ መንግስታዊ አገልግሎቶች፣ ተደራሽ፣ ዘመናዊ፣ ግልጽ፣ ተጠያቂ፣ ቀልጣፋና ተገልጋይን የሚያረኩ ማድረግ ላይ ነዉ፡፡ በዚህም የትኩረት አቅጣጫ ስር የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መንግስታዊ አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክ የተደገፉ ማድረግ፣ የኦን ላይን የህዝብ ማሳተፊያ ስርዓትን መዘርጋት ተቋማዊ ስራዎችን ውጤታማነት ለመለካት የተገልጋይ እርካታንና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ያሳዩትን ለውጥ በሚመለከት በውጪ አካል ማሠራት፣ የከይዘን ስራ አመራር ፍልስፍና አደረጃጀቱን በማጥናትና ባሉበት እንዲኖረው በማድረግ መተግበር፣ የአገልግሎት ስታንዳርድ ማዘጋጀትና ማስተግበር ናቸዉ፡፡

የትኩረት መስክ 3፡ የመልካም አስተዳደርን ማስፈን

የመልካም አስተዳደር የትኩረት መስክ የህዝብ ተጠቃሚነትን፣ እርካታና አመኔታን ለማረጋገጥና ዘለቄታ እንዲኖረው ለማድረግ በዞኑ በየደረጃው ባለው የአስተዳደር እርከን የመንግስት ተቋማትን የዕቅድ ዝግጅት፣ ትግበራና የአፈጻጸም ውጤት ግምገማ ላይ ህዝብን በማሳተፍ፣ የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ማጠናከሪያ የአሠራር ሥርዓቶችን እና ስልቶችን በማስተግበር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትንና ተግባርን በመቀነስ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ነው፡፡ በትኩረት መስኩ ስር የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት የህዝብ ክንፍ ተሳትፎን ማጠናከር፣ የመልካም አስተዳር ችግሮች የሚቀረፉበት የአሰራር ስርዓት ማስተግበር፣ የጸረ ኪራይ ሰብሳቢነትን ትግል ማጠናከር፣ የዜጎች ቅሬታ ማስተናገጃ ስርዓት ማጠናከር ናቸዉ፡፡

የትኩረት መስክ 4፡ የሰዉ ሀብት ልማትና ስራ አመራር ስርዓት ማሻሻል

ዘመናዊ ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሁም ሜሪትን የተከተለ የሰው ሀብት አስተዳደር ስርዓትን በማስፈን ተቋማዊ አፈጻጸምን ማሳደግ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በዚህ የትኩረት አቅጣጫ ስር የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት የሰዉ ሀብት ልማት ተግባራትን በዕቅድ የሚመራበትን ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ፣ በብቃት ላይ የተመሰረተ የሰው ሀይል አሰራር ስርዓቶችን ማስተግበር፣ የሰዉ ሀብት ስራ አመራር ህጎች ትግበራን ማጠናከር፣ የክፍያና የማበረታቻ ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ፣ ልዩ ትኩረት የሚሹ አካላትን ተሳትፎ ማሻሻል፣ የስራ አከባቢ ምቹነትን ማሻሻል፣ የሰዉ ሀብት ስራ አመራር የመረጃ አያያዝና አደረጃጀትን ማሻሻል፣ ስታትስቲካል መረጃ አጠነቃቀርና አቅርቦትን ማሻሻል፣ የመንግስት ሰራተኞች ቅሬታ መመልከትና ዉሳኔ መስጠት እና ዉጤታማ ማድረግ ናቸዉ፡፡

የተቋሙ የልማት ዕቅድ ግቦች

  • ግብ 1የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ በየደረጃው በሚገኙ ተቋማት የአፈፃፀም ዉጤታማነትን ማሳደግ፡በተሸሻለ የዕቅድ የአፈፃፀምና የምዘና መመሪያና ማስተገበሪያ ማኑዋል ላይ ለፐብሊክ ሰርቫንቱ እና ለከፍተኛና መካከለኛ አመራር በአፈጻጸም ስራ አመራር እና ስትራቴጂክ አመራር 940 ለሚሆኑ የክህሎት ስልጠና መስጠት፣ በሁሉም ተቋማት ወጥነት ያለው የቴክኒካል ድጋፍ ማካሄድ እና የድጋፍና ማማከር ክህሎትን በየደረጃዉ ማሳደግ፣ የዕውቅናና የሽልማት መመሪያ በመመሪያው መሰረት እንዲተገብሩ ማድረግ፣ የዕቅድ የአፈፃፀምና የምዘና ትግበራን ክትትልና ግምገማን የማጠናከር ተግባራት ይከናወናሉ፡፡
  • ግብ 2አገልግሎት በስታንዳርድ መሠረት የሚሰጡ ተቋማት ቁጥር በመጨመር የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጣፌን ማሳደግ፡ በወረዱ አሰራሮች መነሻነት የዞኑን የአገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ ለማድረግ አሰራሮችን በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ ማስድረግ፣የተዘጋጁ ስታንዳርዶች በድህነት ቀናሽ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል ተግባራዊ ማስድረግ፣100 ፐርሰንት የመንግሰት ተቋማት የቅሬታ ማስተናገጃ ስርዓት ማስተግበር፣ የኦን ላየን የህዝብ ማሳተፊያ ስርዓትን ማስተግበር፣ ከአገልግሎት አሰጣጥና በመልካም አስተዳደር አንጻር ተቋማዊ ስራዎችን በውጪ አካል ማሠራት፣ የካይዘን ስራ አመራር ፍልስፍና አደረጃጀት ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡
  • ግብ 3የተቋማትን አደረጃጀት ማሻሻል፡ የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ስራዎች ማስተግበር፣ ልዩ ልዩ የጥቅማ ጥቅም እና የትምህርት ደረጃቸውን አሻሽለው ለሚመጡና ከኃላፊነት ለሚነሱ አመራሮች የስራ ስምሪት መስጠት፣ የአገልግሎት ማራዘም ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ ማስቻል፣ ስልጠናዎች መስጠት፣ የምክር አገልግሎቶች ድጋፋዊ ክትትሎችን ወቅታዊ ማድረግና የሰው ሀብት ስራ አመራር አፈጻጸም ክፍተት ዳሰሳ ጥናት ማድረግ ዋና ዋና የተቋማትን አደረጃጀት ማሻሻያ ሥራዎች ተጠናክሮ ይሰራል፡፡ የተቋማዊ ሽግግርና የስራ ሂደት ብስለት መመዘኛ ማኑዋል ተግባራዊ የማድረግ ስራዎች ይተገበራሉ፡፡
  • ግብ 4 – የሴክተር ተኮር የሪፎርም አመራርና ትግበራ ስርዓትን ማጠናከር፡ ሴክተር ተኮር ሪፎርም አመራርና ትግበራ መመሪያና ማስተግበሪያ ማኑዋል ማስተግበር፣ የሴክተር ተኮር ሪፎገርም ትግበራ የውል ስምምነት ሰነድ ተግባራዊ ማድረግ፣ የሲቪል ሰርቪስ ፍኖተ ካርታና የቀጣይ የሪፎርም አተገባበር ሰነዶች ላይ ግንዛቤ መፍጠር፣የመልካም አስተዳደርና የሪፎርም አደረጃጀት ወደ ተቋማት እንዲወር ክትትል በማድረግ የትግበራውን ስራ መፈጸም፣ የክትትል፣ግምገማና ሪፖርት አሰራርን ማጠናከር ይህን ግብ ለማሳካት የሚከናኑ ተግባራት ናቸዉ፡፡
  • ግብ 5ውጤታማ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር፡ በተቋማት፣ስራ ክፍሎች ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓትን ለማስተግበር የአቅም ግንባታ ስራ መስራት፣፣ በሁሉም ተቋማት የዜጎች ቻርተር የአሰራር ስርዓት አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የልምድ ልውውጥ መድረኮችን መፍጠር፣ የስትሪንግ ኮሚቴ መድረክ ማካሄድ፡፡
  • ግብ 6የዜጎች ቅሬታ መስተናገጃ ሥርዓት ትግበራን ማጠናከር፡ ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት ከተገልጋይ አለመርካት የተነሳ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ፈጣን ውጤታማ ምላሽ እንዲያገኙ በአሠራሩ ላይ ሥልጠና መስጠት፣ ትግበራውን መከታተል፣ የምክር አገልግሎት መስጠት፣ በትግበራው ላይ የዳሰሳ ጥናት ማድረግ ግቡን ለማሳካት የተካተቱ ተግባራት ናቸው፡፡
  • ግብ 7የመልካም አስተዳደር ችግሮች መቀነስ፡ የተከለሱ የመልካም አስተዳደር መርሆዎችን ማስተግበር፣ ሥልጠና መስጠት፣፣ ክትትል ማድረግ፣ የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አፈፃፀም ላይ ጥናት ማድረግ፣ የገጠርና የከተማ የመልካም አስተዳደር ፓኬጅ አፈፃፀም መከታተል ድጋፍ ማድረግ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲጠኑ ማድረግ፣ ለተለዩ ችግሮች የመፍቻ ስልትና የማምከኛ ስትራቴጂ መቅረጽ፣ የተሻለ አፈፃፀም መለየት፣መልካም ተሞክሮ መቀመርና ማስፋት፣ ግቡን ለማሳከት የተካተቱ ተግባራት ናቸው፡፡
  • ግብ 8የህዝብ ተሳትፎ ሥርዓት ትግበራን ማጠናከር፡ በመንግስት ተቋማት የህዝብ ተሳትፎ ሥርዓት ትግበራን ለማጠናከር የተዘረጋ የህዝብ ተሳትፎ ሥርዓትን ማስተግበር፣ ህዝቡ በየአደረጃጀቶች እንዲሳተፉ ማድረግ፣ ተቋማት የህዝብ ክንፋቸውን እንዲለዩ ግንዛቤ ማስጨበጥ እና ማስተግበር የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት ፤ድጋፍ ክትትል ማድረግ፣ የተቋማትን የማስፈጸም አቅም በማሳደግ ውጤታማነትንና ተጠያቂነት በህዝቡ የሚረጋገጥበትን ሥርዓት ለማጠናከር የተካተቱ ተግባራት ናቸው፡፡
  • ግብ 9በመንግስት ተቋማት ውስጥ የጸረ-ኪራይ ሰብሳቢነትን ትግል ማጠናከር በመንግስት ተቋማት የፀረ- ኪራይ ሰባሳቢነት ትግል ለማቀጣጠልና ለማጠናከር የተዘረጋ የአሠራር ሥርዓት መተግበር፣ ሥልጠና መስጠት፣ በጥናት የተለዩ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ምንጭ የሆኑ አሠራሮችን በአሠራር፣ በአደረጃጀት ሌሎች ስልቶችን በመንደፍ እንዲዘጉ ማድረግ፣ የተዘጋጁ ማታገያ ሠነዶችን ማስፈጸም፣ የፀረ- ኪራይ ሰባሳቢነት ትግል ማቀጣጠያ መድረኮችን ማዘጋጀት፣ ችግር ውስጥ የገቡትን አካላት ህጋዊና አስተዳራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይህንን ግብ ለማሳካት የተካተቱ ተግባራት ናቸው፡፡
  • ግብ 10የቀበሌ ጽ/ፈት ቤቶችን አደረጃጀትና አሠራር ማሻሻል የቀበሌ ጽህፈት ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማሻሻል የክፍተት ዳሰሳ ጥናት ማድረግ፣በጥናት ግኝት መሠረት የአቅም ግንባታ ስራዎችን መተግበር፣የተከለሱ የቀበሌ መልካም አስተዳደር ፓኬጅ፣ የአገልግሎት አሠጣጥ፣ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ሰነዶችን ተፈጻሚ ማድረግ፣ ድጋፍ ክትትል ማድረግ፣የዕውቅናና የማትጊያ ሥርዓትን መተግበር ግብን ለማሳካት የተካተቱ ተግባራት ሥራዎች ናቸው፡፡
  • ግብ 11የሰው ሃብት ልማት ማሻሻልየተዘረጋውን የሰው ሃብት ልማት የአሰራር ማዕቀፍ መሰረት በማድረግ የሰው ሃብት ልማት ዕቅድ ያዘጋጁ ተቋማትን ማሣደግ፣ በሰው ሃብት ልማት ሥር የተዘጋጁትን፣የህግ ማዕቀፎችን በተቀመጠው ስታንዳድ ልክ ማስተግበር፣ በዞኑ ውስጥ በየደረጃው በሚገኙ ተቋማት የሥልጠና ፍላጎት በበጀት አስፈላጊው እየፈጸሙ መሆኑን ማረጋገጥ፣ የሰው ሀብት ልማት ዕቅድን መሠረት ያደረገ በረዥምና በአጭር ጊዜ ስልጠና የአመራሮችና ፈጻሚዎች አቅም መገንባት፣ በአመራር አቅም ግንባታ ፐሮግራም አመራሮችን ወደ ዩኒቨርሲቲ ማስገባትና ክትትል ማድረግ፣የሴቶች አመራርና ባለሙያዎች አቅም ግንባታ ስልጠና ፕሮግራም ማስተባበር ናቸው፡፡
  • ግብ 12የቀበሌ ሥራ አስኪያጆችን ዕውቀትና ክህሎት ለማሳደግየክህሎት ክፍተት ዳሰሳ ጥናት ማድረግ፣ ክፍተቱን የሚሞላ የዕውቀትና ክህሎት ስልጠና መስጠትና፣ የስልጠና ፋይዳ ጥናት የማድረግ ሥራ ይተገበራል፡፡
  • ግብ 13የሰው ሃብት ስራ አመራር የመረጃ አያያዝና አቅርቦትን ማሻሻል የሰው ሀብት ስታቲስቲካል መረጃ አቅርቦትና ተደራሽነትን ለማሳደግ የ2013 በጀት ዓመት የሰው ሀብት መረጃ በመሰብሰብና በማጠናቀር፣ዓመታዊ የሰው ሀብት ስታቲስቲካል አብስትራክት ማዘጋጀትና በመጽሄት በማሳተም ማሰራጨት ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝና አደረጃጀትን ለማጠናከር፡- የመንግሥት ሠራተኞች መረጃ ኮንቨርት በማድረግ ወደ መረጃ ቋት ኢንኮድ ማድረግ፣ የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ መረጃ አያያዝ ሥርዓት ትግበራ መከታተልና ቴክኒካል ድጋፍ ማድረግ፣ የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ መረጃ አያያዝ ሥርዓት ክልሉ በሚያወርደበት ጊዜ በአዳዲስ ተቋማት መዘርጋትና የማስተግበር ተግባራት የሚፈጸሙ ይሆናል፡፡ የዞኑን የመንግሥት ሠራተኞች መረጃ አያያዝና አደረጃጀት ለማሻሻል፡- አዳዲስ ማኅደራትን በመክፈት በላቴራል ፋይሊንግ ካቢኔት የማደራጀትና የመንግሥት ሠራተኞች የፔርሶኔል መረጃዎችን የተሟሉና ትክክለኛ መሆናቸውን አረጋግጦ በመቀበል የማደራጀት ሥራ ይሰራል፡፡
  • ግብ 14የሰው ሃብት ስራ አመራር ትግበራን ማጠናከር በሰው ሀብት ስራ አመራር ስርዓት ትግበራ የሚታዩትን ሕገወጥ አሠራሮችን ለመቀነስ በየደረጃው ከሚገኙ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ኢንስፔክሽን ሥራ መስራት፣ የሰው ሃብት ስምሪት ክፍተት ዳሰሳ ጥናት ማድረግ፣ የሰው ሃብት ሥምሪት ተገቢነትን ማረጋገጥ፣ በሰው ሃብት ሥራ አመራር አፈጻጸም ላይ መደበኛና ልዩ ምርመራ /ኢንስፔክሽን/ ማከናወንና የዕርምት ዕርምጃ መውሰድ፤ ለሚቀርቡ ቅሬታዎች ተገቢና ወቅታዊ ምላሽ መስጠት፣ ነባርና አዳዲስ የሰው ሃብት ሥምሪት የህግ ማዕቀፎችን ላይ ስልጠና በመስጠት ማስተግበር የፍትሐዊነት ሥራዎችን የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው፡፡ በአዲሱ የነጥብ ሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ዘዴ ድልድል አፈፃፀም በወጡ መመሪያዎችና ሴርኩላሮች አጠቃቀምና በሰው ሀብት አሰራር ሥርዓቶች ላይ ለተቋማት ግንዛቤ መፍጠር፣ በተቋማት በሠራተኛ የተያዙና ያልተያዙ የሥራ መደቦች ለመለየት የዴስክ ኦዲት ማድረግ፣ ከሹመት ለወረዱና ምደባ እንዲሰጣቸው ለሚቀርቡ ባለሙያዎች በጥያቄው መሰረት ክፍት የሥራ መደብ በመፈለግ ምደባ መስጠት፣ የመንግሥት ሠራተኞች በጋብቻ ምክንያት በዞን ውስጥ በሚገኙ ተቋማት የዝውውር አገልግሎት መስጠት፣ዲሎማና ከዲፕሎማ በታች የቅጥር ፍቃድ መስጠት፣በሌላ መልኩ የሚተላለፉ አዳዲስ የትምህርት አይነቶች በተቋማት በስራ ሂደቶቻቸው ጥናት ሰነድ እንደ አግባብነታቸው አካተው እንዲጠቀሙ ሲተላለፍ ተግባራዊ እንዲደረግ ማስቻል፡፡
  • ግብ 15የገጠር ቀበሌ ጽ/ት ቤቶችን አደረጃጀትና አሠራር ለማሻሻል የቀበሌ ጽኅፈት ቤቶችን አደረጃጀትና አሠራር ውጤታማነትን የማሳደግ፣ በፕሮጀክቱ የታቀፉ የገጠር ቀበሌያትን አደረጃጀትና አሰራር የማሻሻል፣ በፕሮጀክቱ የታቀፉ የገጠር ቀበሌያትን አገልግሎት አሠጣጥ ማሻሻል፣ በገጠር ቀበሌ አስተዳደር ስራዎች የአመራሩንና የፈጻሚውን አቅም ማሳደግና በቀበሌ ማጠናከር አፈጻጸም ምርጥ ተሞክሮ በመቀመርና ማስፋት ሥራዎች ተጠናክረው ይሰራሉ፡፡
  • ግብ 16የባለ ብዙ ዘርፍ አካታችነት ጉዳዮችን ማጎልበት በሲቪል ሰርቪሱ የሴቶች እና ህፃናት፣ ኤች አይቪ/ኤድስ፣ አካል ጉዳተኞች ጉዳዮች ተገቢውን ትኩረት አግኝተው ከዋናው የተቋማት ተልዕኮ ጋር ሊከናወኑ በሚችሉበት አሰራር ላይ የሚያተኩር መሆኑን የመከታተልና የመገምገም፣ የግንዛቤ መስጫ መድረኮችን የማካሄድ፣ የተለያዩ የምክር አገልግሎቶችን የመስጠት እና አጠቃላይ በአካታችነት ዙሪያ ተገቢ መረጃዎች እንዲደራጁ የማድረግ እና አስፈላጊ የትግበራ ሰነዶችን ማስፈጸም፣ ማሰራጨት እና በፐብሊክ ሰርቪሱ የሚወጡ የሠው ሀብት ሥራ አመራር የህግ ማዕቀፎች የሴቶችና፣ የአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ያረጋገጡ መሆናቸውን በሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች ዝርዝር መረሀ ግብር ተዘጋጅቶ የሚተገበር ሲሆን በአመራሩ የመከታተል ሥራ ይሰራል፡፡

የተቋሙ አድራሻዎች

  • የመምሪያው ሃላፊ ቢሮ ስልክ ቁጥር 011 330 01 16
  • የሪፎርም ስራዎች ድጋፍና ክትትል ዳይሬ 011 330 25 32
  • የሰው ሃብት ልማት ስራ አመራር ዳይሬ፡ 011 330 04 16
  • የሰ/ሃ/ል/አፈጻጸም ክትትል ዳይሬ 011 330 13 07
  • የመል/አስ/ድ/ክትትል ዳይሬ 011 330 10 61

Comments are closed.