Our Legendary

ሌተናል ጄኔራል ወልደ ስላሴ በረካ ከልጅነት እስከ ወታደራዊ ህይወት
ክቡር ሌ/ጄኔራል ወልደ ስላሴ በረካ በጉራጌ ዞን በቸሀ ወረዳ በሞጨ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ልዩ ስሙ የጥረ በሚባል ስፍራ ህዳር 20 ቀን 1910 ዓ.ም ከአባታቸው ከአቶ በረካ ሱለማና ከእናታቸው ከወይዘሮ ይብወት ብራሮ ተወለዱ፡፡ በአካባቢያቸው በሚገኝ የቤተ ክህነት ትምህርት ቤት የአማርኛን ትምህርት መማር ከጀመሩ በኋላ በ1921 ዓመተ ምህረት የክርስትና አባታቸው በነበሩት በአቶ ጎመሮ ነግዳ አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ መጥተው በልደታ ማርያም ካቶሊክ ሚሲዩን አዳሪ ትምህርት ቤት ገብተው በወቅቱ ይሰጥ የነበረውን የአማርኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋ ትምህርት እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ተከታተሉ በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን በመውረሯ ለሀገር ነፃነት ለመታገል ትምህርታቸውን አቋርጠው በ1929 ዓ.ም ጅቡቲ ተሰደዱ፡፡ እዚያ እንደደረሱም ኢትዮጵያ ውስጥ የጀመሩትን ትምህርት በመቀጠል ጅቡቲ ውስጥ ይገኝ በነበረ የሚሲዩን ትምህርት ቤት ገብተው እውቀታቸውን በማጎልበታቸው በነበራቸው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ችሎታ በመታገዝ በጅቡቲ መንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ አገልግለዋል፡፡ ከዚያም አጴ/ሀይለስላሴ ለስደተኞችና ለአርበኞች ባደረጉት ጥሪ መሰረት በኤደን በኩል ወደ ኬንያ ቀጥሎም ወደ ሱዳን ሄደው ሶባት ላይ በአፄ ሀ/ስላሴ አማካኝነት በጊዚያዊነት በተቋቋመው በቅዱስ ጊዩርጊስ የጦር ትምህርት ቤት ገብተው ወታደራዊ ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡ በመካከሉም የጣሊያን ወራሪ ጦር ድል ተመትቶ በየአቅጣጫው ሲበታተን ከሱዳን ተነስቶ በመተከል በጎጃም አድርጎ ከመጣው የእንግሊዝ የጦር ሚስዮንና የኢትዮጵያ አርበኞች ጋር በመሆን በሰኔ ወር 19 33 ዓ.ም የስደት ትግሉ ተጠናቆ አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላ በሱዳን የጀመሩትን ዘመናዊ ወታደራዊ ትምህርት ለማጠናቀቅ ወደ ሆለታ ገነት ጦር ት/ቤት ተልከው ጥቅምት 1934 ዓ፣ም በምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ ተመረቁ፡፡ በዚያው በተመረቁበት ዓመት በገነት ጦር ት/ቤት ውስጥ አዲስ ተቋቁሞ የነበረው የምድር ጦር የመድፍ ክፍል ወደ አዲስ አበባ ሲዘዋወር እርሳቸውም የክፍሉ አባል ሆነው ተመደቡ ቀጥሎም የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ፀጥታ በሶማሊያ ሰርጎ ገቦች ሲናጋ ፀጥታውን ለማስከበር የተላከው የመድፍ ክፍል አዛዥ ሆነው ሄዱ፡፡ በ1935 ለበላይ መኮንነት በመታጨት ለሲንየር ኦፊሰርነት በተሰጠው ኮርሰ ተካፋይ ሆነው በከፍተኛ ውጤት ተመረቁ ከዚያም ወደ ጦር ሚኒስቴር እንዲዛወሩ በወቅቱ የጦር ሚኒስቴር በነበሩት በክቡር ራስ አበባ አረጋይ ሲታዘዙ እንግሊዛዊው የጦር አዛዥ ትዛዙን በመቃወም ‹‹እርሱ ከተዛወረ የመድፍ ክፍል ይረከቡኝ›› በማለቱ ዝውውሩ ተሰርዞ በክፍላቸው እንዲቆዩ ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁንና የእንግሊዝ የጦር ሚስዩን ስራና ኃላፊነት በ1940 ዓ.ም ያበቃ ስለነበር የመድፍን ክፍሉን የሚመራ ኢትዮጵያዊ መኮንን ለመምረጥ ውድድር ተደርጎ ሌ/ጄኔራል ወልደ ስላሴ ስላሸነፉ በምክትል አዛዥነት ክፍሉን መምራት ጀመሩ፡፡ ከዚያም እንግሊዞች ለቀው ሲወጡ በሌ/ኮሎኔልነት ማዕረግ የመጀመሪያው የመድፈኛ ክፍል አዛዥ ሆኑ፡፡ በ1942 ዓ.ም በተደረገው የአዛዥነትና የመሪነት (command And staff)ኮርስ ተካፋይ ሆነው በከፍተኛ ውጤት አጠናቀቁ፡፡ በ1956 ዓ.ም የግርማዊነታቸው ልዩ ኤታማጆር ሹም እና በዚሁ ዓመት የምድር ጦር ምክትል አዛዥ ሆነው ተሾሙ በዚያው አመት በኦጋዴን ጠረፍ አካባቢዎች/ በየጉርጉር ብየቆሪ ተፈሪበር ኢነጎሩ ደበ/ጎራሌ ላይ ከሱማሊያ ወታደሮች ጋር በተደረገው ጦርነት ዘመቻውን እንዲመሩና በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀባቸው ግዛቶች የበላይ አስተዳዳሪ ሆነው ተመደቡ ከዚያም እንደተመለሱ የመከላከያ ሚኒስቴር ኢንስፔክተር ጀኔራል በ1957 ዓ.ም የጦር ሀይሎች ኤታማጆር ሹመት አገኙ፡፡ ጳጉሜ 4 ቀን 1962 ዓ.ም የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒሰትር ዴኤታ በየካቲት 1966 ዓ.ም የምድር ጦር ዋና አዛዥ በተከታታይ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም ሲሆኑ በ1966 ሰኔ ወር ደግሞ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሆነው ተሹመዋል ሌ/ጄኔራል ወ/ስላሴ በወታደርነት ሙያቸው ከእጩ መኮንነት በመነሳት በተከታታይ ባገኙት የማዕረግ እድገት በኢትዮጵያ ወታደራዊ እድገት እርከን በዘመኑ የተደረሰበትን የመጨረሻውን ከፍተኛ እድገት እርከን በዘመኑ የተደረሰበትን የመጨረሻውን ከፍተኛ የእድገት ደረጃ የሌ/ጄኔራልነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ ክቡርነታቸው ከመደበኛ ስራቸው ጎን ለጎን በማህበራዊ በኢኮኖሚያዊ በፖለቲካዊ መስኮች በመሳተፍ በአርአያነት የሚጠቀሱ ተግባራትን አከናውነዋል በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውንና በጉራጌ ህብረተሰብ ጠንሳሽነት የተቋቋመውን ህዝባዊ ራስ አገዝ የልማት ድርጅት በብቃት በመምራትና የተግባር እቅድ በመንደፍ ድርጅቱ በሀገር ውስጥና በውጪ አለም ጭምር ከፍተኛ ዝና እንዲጎናጸፍ አድርገዋል፡፡ ሌሎች ተወላጆችን ከጎናቸው በማሰለፍና የህዝቡን አቅም በማስተባበር በተቀናጀ ጥረት ተወላጁን የሚያኮራ ተጨባጭ ውጤት በማስገኘት ጥረት ትውልዱን ያኮራ ተጨበጫ ውጤት በማስገኘት የጉራጌን ህብረተሰብ ታታሪነትና ስራ ወዳድነት በተግባር አሳይተዋል፡፡ በክልሉ ትምህርት ቤቶችና የህክምና ተቋማት እንዲቋቋሙና እንዲስፋፉ በማበረታታት እንዲሁም ህዝቡ ባህሉን እንዲያውቅና አጠናክሮ እንዲይዝ በመምከር የጉራጌ ብሔረሰብ እርስ በእርስ የመተጋገዝ ራስን የመቻል ጥረቱን እንዲያዳብርና ፈር ይዞ እንዲጓዝ ከፈ ያለ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በፖለቲካው መስክ ቀደም ሲል በክፍለ ሀገር አስተዳዳሪነትና በህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልነት ካከናወኗቸው ስራዎች በተጨማሪ በ1983 ዓ.ም በተፈጠረው ለውጥ ብሔር ብሔረሰቦች የፖለቲካ ድርጅቶችን እንዲያቋቁሙ ባስፈለገበት ወቅት የቤተ ጉራጌ ህዝብ ማንነቶችን ለማሳወቅና ለማህበራዊ ፣ለኢኮኖሚያዊና ለፖለቲካዊ መብቶች ለመታገል የሚያስችል የፖለቲካ ድርጅት ለመፍጠር በተደረገው እንቅስቃሴዎች የጉራጌ ብሔረሰብ ለኢትዮጵያ አንድነት ያለውን የማያወላውል ቆራጥ አቋም ሰላማዊነት ለወገን አሳቢነትና ተቆርቋሪነት አንጸባርቀዋል፡፡ የኑሯቸው ስነ-ምግባርም በትምህርት ሰጪነቱ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የነበራቸው ከፍተኛ የመንግስት ሹመት ሳያግዳቸው ከደሀው ወገናቸው ጋር ተሰልፈው ሰርተዋል፡፡ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የእረፍት ጊዜያቸውን ጭምር ለህዝብ ልማት ከማዋላቸውም በላይ የተሰጣቸውን ሹመትና ስልጣን፣የህዝብ ፣የመንግስት ሃብትና ንብረት ለሀገርና ለወገን ጥቅም በማዋል የጉራጌን ብሔረሰብ ከፍተኛ ሞራልና ታማኝነት አስመስክረዋል፡፡ በአጠቃላይ ኑሯቸውንና ምርቶቻቸውን በታማኝነት ለሀገር ለወገን ጥቅም ሰውተዋል፡፡ ክቡር ሌ/ጄኔራል ወልደ ስላሴ በረካ ከዚህ በላይ በአጭሩ በተጠቀሱት የሥራ ውጤቶቻቸው የጉራጌን ብሔረሰብ አውቀውም ሆነ ሳያውቁት ዝቅ አድርገው ሲመለከቱ የነበሩትን ወገኖች አስተሳሰብ ለማስለወጥና የጉራጌ ህዝብ በማናቸውም መስክ ከማንኛውም ኢትዮጵያ ህዝብ እኩል የተመጣጠነ ብቃት እንዳለው ለማረጋገጥ የቻሉ የመላው ጉራጌ ልጅ ናቸው፡፡
ምንጭ ክቡር ሌ/ጄኔራል ወልደ ስላሴ በረካ (1910-2002)

Comments are closed.