Gurage zone Admin Message


አቶ መሀመድ ጀማል
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ

አሁን በደረስንበት የእድገት ደረጃ የመረጃ አስፈላጊነትና ጥቅም እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ግልፅ ነው። በዘመነ ግሎባላይዜሽን ዋነኛ የመወዳደሪያ መሳረያ እየሆነ ያለው መረጃ ነው። ትክክለኛና ጥራት ያለው መረጃ ማደራጀት፣ መተንተን እንዲሁም ለሁሉም መረጃ ፈላጊ አካላቶች ተደራሽ አንዲሆን ማስቻል ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን ወሳኙ ቅድመ ሁኔታ ነው።
ይህንን ታሳቢ በማድረግ የጉራጌ ዞን አስተዳደር የዞኑን ሁለንትናዊ ልማትና ዕድገት ለማፋጠን ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪ ሀገር ላሉ በዞኑ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ፣ በዞኑ በኢኮኖሚ፣በማህበራዊ፣ በባህላዊ ልማቶች ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉና በየትኛውም ቦታ ሆኖ ስለዞኑ መረጃ ለሚፈልጉ ሁሉ ተደራሽ መሆን በሚያስችል አግባብ ዞናዊ ድህረ-ገፅ ተከፍቶዋል። በዚህ ድህረ ገፅ ስለዞናችን አጠቃላይ በሁሉም ዘርፎች ያሉ ጥሬ መረጃዎች፣ የተተነተኑ መረጃዎች በአግባቡ ተሰድሮ ቀርቦዋል።
የጉራጌ ዞን ጢያ ትክል ድንጋይ፣ የአብሬት ሼህ መስጂድ፣ ሙህር አኮሊል እየሱስ ገዳም የመሰሉ እጅግ አስደናቂ የሆኑ የሚዳሰሱ እንዲሁም የመስቀል ወኸመያ፣ የአብሬት ሞሊድ፣ የሰርግ ስነስርአት፣ የለቅሶ ስነስርአትና መሰል የማይዳሰሱ ቅርሶች፣ እጅግ የሚያስደሞሙ ባህላዊ የዳኝነትና የሽምግልና ስርአቶች፣ ውብና ቀልብ ሳቢ ባህላዊ ውዝዋዜዎች፣ የተመጣጠነና ምቹ የአየር ንብረት፣ 167 ሜጋ ዋት በላይ የማመንጨት አቅም እንዳለው በጥናት ከተረጋገጠው የዋቤ ወንዝ ጀምሮ አመት በሙሉ የሚፈሱ ለመስኖ ልማት መዋል የሚችሉ ከ10 በላይ ትላልቅ ወንዞች፣ ጥቅጥቅ ደኖች፣ ከሰንሳላታማው የዘቢደር ተራራ እስከ ጊቤ ሸለቆ ፓርክ ማራኪ መልካዓ ምድር፣ ለሰብል ልማት፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ ለቡና ለቅመማ ቅመም ልማት፣ ለእንስሳት ልማት እጅግ ምቹ የአየር ንብረትና ሰፊ ሊለማ የሚችል መሬት እንዲሁም ታታሪና ስራ ወዳድ ህዝቦች የታደለች ዞን ናት።
በዞናችን ሶስት የመብራት ሀይል sub-power stations ( ወልቂጤ፣ ቡታጅራ፣ ቡኢ) ፣ 8 የመብራት አገልግሎት ማዕከላት ( ወልቂጤ፣ ጉንችሬ፣ እምድብር፣ አገና፣ አረቅጥ፣ ሀዋሪያት፣ ቡታ ጅራና ቡኢ) እንዲሁም ከሁሉም ከተሞች በተጨማሪ 110 የገጠር ቀበሌዎች የመብራት ሀይል ተጠቃሚ ሆነዋል። በሁሉም የዞናችን አካባቢዎች የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽ ሆኖዋል።
የዞናችን መዲና የሆነችው ወልቂጤ ከተማ አቋርጦ የሚያልፈው የአዲስ አበባ-ጅማ -ጋንቤላ ቦንጋ ሚዛን ቴፒ አስፋልት በመንገድ በተጨማሪ የወልቂጤ -ሆሳና፣ የጉብሬ – ቡታ ጅራ ፣ ቡኢ፣ ኬላንና ቡታጀራ ከተማን አቋርጦ የሚያልፈው የአዲስ አበባ- ሆሳና-ወላይታ ሶዶ–አርባምንጭ አስፋልት መንገድ፣ የቡታ ጅራ -ዝዋይ አስፋልት መንገድ እንዲሁም ግንባታ ላይ ያለው የአጣጥ ማዞረያ-ጉንችሬ- ቆሴ-ጌጃ–ሌራ አስፋልት መንገድ ዞናችን በአራቱም አቅጣጫ ምቹ የትራንስፖርት አማራጮች ያሉዋት መሆኑ አመላካች ናቸው። በተጨማሪም የትራንስፖርት አገልግሎቱን የሚያሳልጡ በክልሉ የገጠር መንገድ፣ በቀበሌ ተደራሽ መንገድ ፕሮጀክት እንዲሁም በባለሀብቱና በማህበረሰቡ የተገነቡ በርካታ የውስጥ ለውስጥ የጠጠር መንገዶች አሉ።

በአጠቃላይ የአፍሪካ መዲናና በአፍሪካ ትልቁን የገበያ ማዕከል በውስጧ ከያዘችው አዲስ አበባ በቅርብ ዕርቀት ላይ የምትገኝ ዞን መሆኗ ዞናችን በግብርና ልማት ማለትም በሰብል ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቡና በቅመማ ቅመም፣ በእንስሳት ልማት፣ በማኑፋክቸሪንግና በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በአገልግሎትና በቱሪዝም ልማት ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ እጅግ ተመራጭ ያደርጋታል።
ይህንን ድህረ-ገፅ ማበልፅግ ያስፈለገዉም በየትኛም የልማት ዘርፍ ላይ ኢንቬስት ማድረግ ለምትፈልጉ በሀገር ውስጥም ሆነ ውጪ ሀገር ያላቹ ሁሉ ወደ ዞናችን መምጣት ሳያስፈልጋቹ ባላቹበት ቦታ ሆናቹ የምትፈልጉትን መረጃ በቀላሉ እንድታገኙ ለማስቻል ነው። በተጨማሪም የምርምር ማዕከላት፤ ተመራማሪዎች፤መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች፤ ኢንቬስተሮች፤ የሀገር ዉስጥና የዉጪ ሚድያዎች፤ ጋዜጠኞች፤ ዜጎች ድህረ-ፃችንን በመጠቀም ስለዞናችን ትክክለኛ፤ አስተማማኝና ወቅታዊ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነዉ ፡፡
በአጠቃላይ ይህ ድህረ-ገፅ በጊዜ ሂደት አዳዲስ የሚጨመሩና የሚሻሻሉ ነገሮች እንዳሉ ሆነዉ አሁን ባለንበት በሁሉም ዘርፍ ላይ ትክክለኛና ጥራት ያላቸዉ መረጃዎች በተሟላ ደረጃ እንዲኖረዉ ለማድረግ ጥረት ተደርጎዋል፡፡ በመሆኑም ድህረ-ገፁን ለሚጠቀሙ ሁሉ ስለዞናችን ትክክለኛ፤ አስተማማኝና ወቅታዊ መረጃዎችን ማግኘት የምትችሉ መሆኑ በአክብሮት ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡

Comments are closed.