የጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ የ2017 ዓ.ም የ1ኛ ሩብ አመት እቅድ አፈጻጸም ከፖሊስ አባላትና ከሚመለከታቸዉ ባለ ድርሻ አካላት በወልቂጤ ከተማ ገምግሟል።

የጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ገና ደገሙ እንዳሉት በዞኑ የሚፈለገዉ ሰላም እንዲመጣ ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።

ባለፉት ሶስት ወራት የጸጥታ አካሉ ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን በተሰሩ ስራዎች አበረታች ዉጤት የታየበትና ይህንንም የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አብራርተዋል።

ማህበረሰቡ አካባቢዉን ለመጠበቅ ሮንድ መዉጣት እንዳለበት፣ አምፖል የማዉጣት እንዲሁም የጸጉረ ለዉጥ እንቅስቃሴ ለመከላከል በሁሉም አካባቢዎች የቅስቀሳዉ ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

አበሽጌ ወረዳ አካባቢ የነበረዉ የጸጥታ ችግር ለመከላከል ከኦሮሚያ ክልል ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑም ያመላከቱት ዋና ኢንስፔክተር ማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ስራዉ አጠናክሮ በማስቀጠል በዘርፉ የሚፈለገዉን ዉጤት ማምጣት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረቡት የጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ የልማት እቅድና ኢኮኖሚ ዲቪዥን ሀላፊ ኮማንደር ሰለሞን መርሻ እንዳሉት የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ትምህርት ሽፋን ለማሳደግ በተሰራዉ ስራ ለ183 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ መፍጠር እንደታቸለም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በተለያዩ አደረጃጀቶች ተደራጅተዉ የተከሰቱ የወንጀል ድርጊቶች ለመከላከል ከመንግስት ጎን በመሆን ወንጀል በመከላከል ረገድ ዉጤታማ ስራዎች እየሰሩ እንደሆነም አብራርተዋል።

በተለያዩ የዞኑ አካባቢዎች በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ማለትም 8 ክላሽ ፣ 57 የክላሽ ጥይት ፣ 1 ኤስ ኬኤስ፣ 116 ጥይት፣ 4 ቦንብ 1 ሽጉጥና ሁለት ሰዎች በድርጊቱ ተጠርጥረዉ ምርመራቸዉ እየተጣራ መሆኑም አስታዉሰዋል።

የዞኑ ሰላም ለማስፈን አቃቤ ህግ ፖሊስና ማህበረሰቡ ተቀናጅቶ መስራት እንዳለበትና በዘርፉ ዉጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

በአፈጻጸም መድረኩ የተገኙ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት በሩብ አመቱ የተሰሩ ስራዎች የሚበረታታና የሮንድ ጥበቃ ጋር በአንዳንድ አካባቢዎች ክፍተት መኖሩም አንስተዉ ለዚህም ትኩረት ቢሰጠዉና ግጭቶች እንዳይፈጠሩ በቅንጅት መሰራት እንዳለበትም አመላክተዋል።

ፖሊስ በበአላትና ሌሎችም ኹነቶች ሲፈጠሩ ሰላም ለማስፈን እየሰራዉ ያለዉን ስራ የሚበረታታ እንደሆነም አስረድተዋል።

በየአካባቢ የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ለመቅረፍ በቅንጅት መሰራት አለበት ያሉት አስተያየት ሰጪዎች በተለያዩ ቦታዎች አንዳንድ ወጣቶች በህገወጥ መንገድ የባጃጅ ተሽከርካሪ እያስቆሙ ገንዘብ የሚቀበሉ ያሉ ሲሆን እነዚህም የሚመለከታቸዉ አካላት ሊያስቆሙ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የጸጥታ ሀይሉና ማህበሰቡን በማቀናጀት የዞኑን ሰላም በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አብራርተዉ በየአካባቢዉ የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች በህገወጦችና ሌቦች እንዳይሰረቁና እንዳይቆረጡ ፖሊስ በጋራ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።

አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣ እየተሰራ ያለዉ ስራ የሚበረታታ እንደሆነም አንስተዉ በአበሽጌ ወረዳና በወልቂጤ ከተማ አካባቢዎች ህገወጥ የጦር መሳሪያ የቁጥጥርና የክትትል ስራዉ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *