በጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳደር እና የግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ አበራ ወንድሙ አቅራቢነት አቶ ሙራድ ከድር በእጩነት ቀርበው የምክር ቤት አባሉ በሙሉ ድምፅ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ተጠባባቂ ከንቲባ አድርጎ ሾሟል።
አቶ ሙራድ ከድር በጉራጌ በዞንና በወረዳ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት በከፍተኛና በመካከለኛ የስራ ሀላፊነት ህዝብ ሲያገለግሉ የቆዩና በነበራቸው የስራ ቆይታ መልካም አፈፃፀም የነበራቸው ሲሆን በዛሬው እለት አቶ ሙራድ ከድር የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ተጠባባቂ ከንቲባ አድርጎ የምክር ቤት አባሉ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
አቶ ሙራድ ከድር ባደረጉት ንግግር ወልቂጤ ከተማ የብዙ ታሪኮችና የልማት እድሎች ባለቤት ፣ የታታሪዎችና የስራ ወዳዶች መፍለቂያ እንዲሁም የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መኖርያና የንግድ ኮሪደርና ከሀገራችን ከተለያዩ ክፍሎች የሚቀሳቀሱ እንግዶች ማረፊያ የሆነችው ከተማችን ካሏት ምቹ እድሎች አኳያ አቻ ከተሞች ከደረሱበት የእድገት ደረጃና ተወዳዳሪ እንድትሆን ሁሉም በቅንጅት ሊሰራና ሊያግዝ ይገባል ብለዋል።
በከተማዋ የሚስተዋሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሰላምና የደህንነት ማስፈን፣ የህግ የበላይነት ማስከበር፣ የነቃ የማህበረሰብ የልማት ተሳትፎ በመፍጠር እና እኔነት ይልቅ እኛነት በማስቀደም ለከተማዋ ሁለንተናዊ ለውጥ ሁሉም በጋራ መስራት መቻል አለበት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል ።
በዛሬው አስቸኳይ ጉባኤ በተመሳሳይ አቶ ታደለ በቀለ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ዋና የመንግስት ተጠሪ አድርጎ የሾመ ሲሆን ሹመቱም ለምክር ቤት አባላት ቀርቦ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
መረጃው የወልቂጤ ከተማ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ነው