ሰልጣኝ አመራሮች በመስክ ምልከታው ወቅት ያዩትን ምርጥ ተሞክሮ በማስፋት የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መስራት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል ገለጹ።


ሰልጣኝ አመራሮች በመስክ ምልከታው ወቅት ያዩትን ምርጥ ተሞክሮ በማስፋት የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መስራት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል ገለጹ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ወልቂጤ ማዕከል 3ኛ ዙር የአቅም ግንባታ ሰልጣኝ አመራሮች በጉራጌ ዞን ጌታ ወረዳ ሰነንና ቆረፍቻ ቀበሌ በኩታ ገጠም የለማው የገብስ ማሳ ምልከታ አድርገዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ሶስተኛ ዙር ሰልጣኝ አመራሮች “የህልም ጉልበት ለእምርታዊ እድገት” በሚል በወልቂጤ ማዕከል የአቅም ግንባታ ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።

የጉራጌ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል በመስክ ምልከታው ወቅት እንዳሉት በወረዳው ሰልጣኝ አመራሮች በስልጠናው ወቅት በንድፈ ሀሳብ እየወሰዱት ያለው ስልጠና በተጨባጭ መሬት ላይ መኖሩን በማየት ተግባሩ ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ ነው።

በዘንድሮ አመት በዞኑ ታርሰው የማይታወቁ ከ5ሺህ 4መቶ ሄክታር መሬት በማረስ ወደ ሰብል መቀየር መቻሉን ያነሱት አቶ አለማየሁ ከነዚህም በጌታ ወረዳ ሰነንና ቆረፍቻ ቀበሌ በ103 ሄክታር መሬት የለማው የገብስ ማሳ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

አካባቢው ከፍተኛ አሲዳማ መሆኑን አንስተው ለዚህም ማሳው በኖራ በማከም በተሰራው ስራ ሰብሉ በምርጥ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በግብርናው ዘርፍ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ያነሱት አቶ አለማየሁ ሰልጣኝ አመራሮችም በመስክ ምልከታው ያገኙትን ምርጥ ተሞክሮ ወደ አካባቢያቸው በመውሰድ ይበልጥ አስፍተው በመስራት የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የጌታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በህሩ ኸይረዲን በበኩላቸው የመስክ ምልከታ እየተደረገበት ያለው ማሳ ከዚህ ቀደም ቦታው ለረጅም አመታት ታጥሮ የነበረና የተጎዳ መሬት እንደነበር ጠቅሰው የአፍርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከመስራት ባለፈ ከወልቂጤ ግብርና ማዕከል በመቀናጀት በኖራ በማከም በሰብል እንዲለማ ማድረግ ተችሏል።

በወረዳው ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ተግባር በቀጣይም ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

ከለማው ማሳ በሄክታር ከ43 ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

በወረዳው በሰነንና ቆረፍቻ ቀበሌ 3መቶ 88 ወጣቶች፣ አርሶ አደሮችና ሴቶች በ103 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በገብስ መልማቱንም ተናግረዋል።

ምርቱ ሳይባክን ለመሰብሰብ የኮምባይነር አቅርቦት እንዲኖር የወረዳው አርሶ አደሮች መጠየቃቸውን ገልጸው ለዚህም የወረዳው መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ አንስተዋል።

በመስክ ምልከታው የተሳተፉ አመራሮች እንዳሉት በወረዳው ወጣቶች፣ አርሶ አደሮችና ሴቶች በማህበር በኩታ ገጠም ያለሙት ማሳ አድንቀዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ሉአላዊነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ያለው ስራ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው ይህም በቀጣይም ይበልጥ አጠናክረው እንደሚሰሩ ነው ያነሱት።

በመስክ ምልከታው ወቅት ያዩትን ምርጥ ተሞክሮ ወደ አካባቢያቸው በመውሰድ አስፍተው እንደሚሰሩም አንስተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *