በጌታ ወረዳ የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ስራ አጥነትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ የወረዳው ስራ እድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽ/ቤት አስታወቀ።

በተመቻቸላቸው የስራ እድል ውጤታማ መሆናቸው በወረዳው በተለያዩ ዘርፎች በማህበር ተደራጅተው የሚሰሩ ወጣቶች ተናግረዋል።

በአመቱ 5 ሺ 7 መቶ ወጣቶች በጊዜያዊ እና በቋሚነት የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ በሩብ አመቱ 2ሺ 6መቶ 57 ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩ ተገልጿል።

የጌታ ወረዳ ስራ እድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አክመል ተካ እንደገለፁት በወረዳው የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ እየተሰራ ነው።

ወጣቶቹ በገጠርና በከተማ በበሬ ድለባ ፣በሰብል ልማት ፣በዶሮ እርባታ ፣በንብ ማነብ ፣ በምግብ ቤት ፣በብረታ ብረት፣በእንጨት ስራ፣በኮንስትራክሽንና በኮንስትራክሽን ግብዓት አቅርቦት እና በሌሎች ተግባራቶች ላይ ወጣቶቹ ተደራጅተው እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

አቶ አክመል አክለውም በ2017 ዓ.ም ለተደራጁ ወጣቶች በከተማና በገጠር 3 ሚሊየን 8 መቶ ሺ ብር ማሰራጨት የተቻለ ሲሆን በቁጠባ ሞቢላይዜሽን ደግሞ እስካሁን 1 ሚሊየን 8 መቶ ሺ 7 መቶ 96 ብር መቆጠባቸው ተናግረዋል።

ከ10 ሚሊየን 9 መቶ 74 ሺ ብር በላይ ብድር ለማስመለስ ታቅዶ እስካሁን 3 ሚሊየን 104 ሺ ብር መመለሱ አብራርተዋል።

ወጣቶቹ ጥራት ያለው ስራ ሰርተው በገበያ ተወዳዳሪ እና ትርፋማ እንዲሆኑ በተሰራው ስራ ብዙ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች ማፍራት መቻሉ የገለጹት ኃላፊው የሚገጥማቸው የመሰረተ ልማት ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቅንጀት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የገበያ ትስስር እንዲያገኙ በሚወጡ ጨረታዎች እንዲሳተፉ የማድረግ ፣መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የማስተሳሰር፣ምቹ የመሸጫ ቦታዎች የማመቻቸት እና ምርታቸው እንዲተዋወቅ እየተሰራ ነው ብለዋል አቶ አክመል ተካ።

የጽ/ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ልራጎ በበኩላቸው ወጣቱ አልባሌ ቦታ ከመዋል እና ስራ እየጠበቀ ከሰው ጥገኛ ከመሆን ይልቅ ስራ ሳይንቅ ወደ ስራ ገብቶ የራሱም ሆነ የቤተሰቡ ህይወት ሊቀይር ይገባል።

በመሆኑም ተቋሙም ኢንተርፕራይዞች በተሰማሩበት የሙያ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ እና ክትትል የማድረግ፣ የክህሎት ስልጠና የመስጠት፣መሰረተ ልማት የመዘርጋት ፣የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ እና እንዲቆጥቡ ይሰራል ነው ያሉት።

አቶ ደሳለኝ አክለውም ወጣቶቹ በከተማና በገጠር ዘርፍ በማኑፋክቸሪንግ፣በአገልግሎት ዘርፍ፣በኢንዱስትሪ ፣በግብርና እና በሌሎችም ዘርፍ ተሰማርተው እንደሚገኙ አስገንዝበዋል።

ለአብነትም በገጠር ግብርና 1መቶ 30 ሄክታር መሬት በወጣቶች ሰብል ምርት እንደተሸፈነ አንስተው ይህ ደግሞ ምርቱ ከራሳቸው አልፎ ለህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ አቶ ደሳለኝ ተናግረዋል።

ወጣት ኑር አወል ፣ወጣት ቋሲም ጀማል ፣ወጣት በጋራ በሰጡት ሀሳብ ከዚህ በፊት ስራ ጠባቂዎች በመሆናቸው ከቤተሰባቸው ጥገኛ እንዲሆኑ ዳርጎዋቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ በግል እና በመንግስት ተነሳሽነት መጀመሪያ በትንሹ ቁጠባ ጀምረው መንግስት ደግሞ ብድርና ቦታ በማመቻቸቱ አሁን ግን የኢኮኖሚ አቅማቸው እያሳደጉ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህም በሚሰጡት አገልግሎት እራሳቸው ከመለወጥ በተጨማሪ በሙያቸው ቤተሰባቸው አልፎም ህብረተሰቡ እንዲጠቀም እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

ወጣቶቹ አክለውም መንግስት የሚገጥማቸው ችግር ከመቅረፍ ፣ ከመደገፍ ፣ብድር እና ቦታ ከማመቻቸት እና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች ከመፍጠር አንጻር አበረታች መሆኑን አንስተው የመብራት መቆራረጥ ችግር እንዲቀረፍላቸው እና ተጨማሪ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ወጣቶቹ ጠይቀዋል።

ወጣቶች ስራን ከማማረጥና ስራን ከመናቅ ይልቅ ስራ ፈጣሪ በመሆን እራሳቸው ፣ቤተሰባቸው እና ሀገራቸው እንዲቀይሩ ምክር ለግሰዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *