የዋቤ ወንዝ በወፍ በረር!!

ጉራጌ ዞን ለመዝናኛ፣ ለምርምር ወይም የራስ የጥሞና ጊዜ ለመውሰድ የሚያገለግሉ በርካታ የቱሪዝም ሀብት መገኛ ነው።

ከነዚህም የቱሪዝም መስህቦች መካከል አንዱ የዋቤ ወንዝ ነው፡፡የዋቤ ወንዝ ከተፈጥሮ ደኖች ጋር ተዋህዶ አካባቢዉ ለአይን የሚማርክና ሳቢ አድርጎታል።

የዋቤ ወንዝ ከወልቂጤ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ተፈጥሮአዊ መስህብ ነው፡፡ ይህ አከባቢ አእዋፋት፣ የዱር እንስሳትና እድሜ ጠገብ የሆኑ የተፈጥሮ ደኖች የሚገኙበት ማራኪ ስፍራ ነው፡፡

በተጨማሪም የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ ውጤት የሆነው የዋቤ ወንዝ ላይ የተሰራው ታሪካዊ የብረት ድልድይ መገኛ ቦታ በመሆኑ ስፍራዉ ካለው ታሪካዊ ዳራ እንፃር ተገቢውን ትኩረት ተሰጥቶት ለመናፈሻነት፣ ለሎጅ፣ ለዘመናዊ መስኖ፣ ለአሳ እርባታ፣ ለኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ፣ ለኢኮ ቱሪዝም በተፈጥሮ የታደለ ምቹ መልካዓምድር ያለው ቦታ ነው፡፡

የዋቤ ወንዝ ከጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ለጎብኚዎች ተመራጭ ስፍራ ለመሆን ከፍተኛ ዕድል ያለው ቦታ ነው፡፡የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ የተለያዩ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ሀብቶች፣ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው የዱር እንስሳት፣ አእዋፋት እንዲሁም ማራኪና ተፈጥሮአዊ መልካዓ ምድር፣ ሰው ሰራሽ ዋሻዎች፣ በቁጥር 40 የሚሆኑ ፍል ውሃዎች፣ አመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች እንዲሁም ብዙ ጥናት የሚያስፈልጋቸው የቱሪዝም ሀብቶች የታደለ ፓርክ ነው፡፡

ጉራጌ ዞን በቱሪዝም ዘርፍ እምቅ ሀብት ያለዉና በዉብ የተፈጥሮ ሀብት፣ በአኩሪ ባህልና ታሪክ የተምነሸነሸ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚገዙ በአለም አቀፍ ደረጃ እ.አ.አ በ1980 በUNESCO የተመዘገበው የጢያ ትክል ድንጋይ ጨምሮ ጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ፣ ለአይን ማራኪ በርካታ ቁጥር ያላቸዉ አእዋፋት ፣ የዱር እንስሳት ፣የተፈጥሮ ደኖች ፣ ፣ፉል ዉሃዎች ፣ የተለያዩ ለአይን ማራኪ የሆኑ የተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ጸጋዎች ከምቹ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥና የአየር ፀባይ ጋር ተዳምሮ ልዩ መንፈስ እርካታን የሚያጎናጽፍ ጸጋዎች ይገኛሉ፡፡

ከነዚህም ሀብቶቿ አንፃር ሰሞኑ ወደ ዞናችን የመጣዉ ኢትዮ ራፍቲንግና ሃይኪንግ አስጎብኚ ድርጅት ዋቤ ወንዝ ላይ የውሃ ቀዘፋ(ራፍቲንግ) እና የእግር ጉዞ (የሃይኪንግ) ጉብኝት አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ሀገራት ጋር ስትወዳደር በቱሪስት ተመራጭ ለመሆን ከሚያስችሏት ነገሮች መካከል አንዱ የባህል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮ ሀብት መስህቦቿ እና አስተማማኝ ደህንነት ያላት በመሆኑን ነው።

በጉራጌ ዞን ከሚገኙ የቱሪዝም መስህቦች መካከል እስካሁን ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች ብቻ እየተጎበኘ ሲሆን ከተፈጥሮአዊ መስህቦች አንፃር ክፍተቶች አሉ፡፡ ይህንን ለመቀየር አዲስ አበባን ማዕከል ያደረጉ አስጎብኚ ማህበራት በባለፉት 5 ወራት ለ3ኛ ዙር ወደ ዞኑ በመምጣት ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህም ለዞኑ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ግልፅ ነው ።

ዞኑ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ፣ ምቹ የአየር ፀባይ፣ መልካም የእንግዳ አቀባበል ባህል ያለው ማህበረሰብና በርካታ የቱሪዝም መስህቦች ያሉበት በመሆኑ
አስጎብኚ ማህበራትና ቱሪስቶች መምጣታቸው ያሉን የቱሪዝም መስህቦች ለማስተዋወቅና የቱሪዝም መስኩ ለማነቃቃት ያለመ መሆኑን በጉራጌ ዞን የቱሪዝም መስብ ልማት ቡድን መሪ አቶ ከተማ ሀይሉ መላክቷል።

እንደ ከተማ አለሙ ገለፃ ዋቤ ወንዝን ሰው ሲወስድና ሲበላ የነበረበት ታሪክ ቀይሮ አሁን ላይ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆኑ ለአከባቢው ማህበረሰብ የስራ እድል ከመፍጠር አንፃር ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።

አቶ አሸናፊ ካሳ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ሲሆኑ እንዲህ አይነቱ ጉብኝቶች ያላቸው ፋይዳ ምንድነው በተለይም አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ከመፍጠር አንፃር ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄ እንዲህ ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ አንደኛ ለአከባቢው ማህበረሰብ ወይም ለጎብኚው አማራጮችን ለመፍጠር ያግዛል፣ የአከባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን ማለትም የስራ እድል ለመፍጠር፣ በአከባቢው የሚገኙ ዞኖችም ወደ እንቅስቃሴ እንዲገቡና መንግስት ፖሊሲዎችና ህጎቹ እንዲመለከትና እንዲከልስ ያደርጋልም ብለዋል፡፡

የቱሪዝም ዘርፉ በሀገር ግንባታ ላይ በቱሪዝም ዘርፍ የሚሰሩ አስጎብኚ ድርጅቶች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች የማስተዋወቅ ስራ መጠናከር አለበት።

የዞኑ ባህል ቱሪዝም ተቋም ከሚዲያዎች በመቀናጀት ያልተዳሰሱ የቱሪዝም መስህቦች በደንብ እንዲተዋወቁ ማድረግ እንዳለበት አንስተው ባለሀብቶችም በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ መደረግ አለበትም ብለዋል።

ዋቤ ወንዝን በሚጎበኙበት ወቅት ቦታው ምቹ ካለመሆኑ የተነሳ ጀልባ ለማስገባትና ለማስወጣት መቸገራቸውን ገልፀው የዞኑ መንግስት በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ትኩረት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል።

ጉራጌ ዞን ለ3ኛ ጊዜ መጎብኘታቸውን የገለፁት አቶ ሳሙኤል ካሳ ዋቤ ወንዝን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደጎበኙና አከባቢው ላይ ያለው መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ ለቱሪስት የሚማርክ በመሆኑ ተፈጥሮአዊነቱን ጠብቆ ለማቆየት ቦታው እንዲለማ ቢሰራ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት የአከባቢው ማህበረሰብም ላደረገላቸው እንክብካቤ ልዩ ምስጋና አቅርበዋል።

እኛም የዚህ ጹሁፍ አዘጋጆች የዋቤ ወንዝና የተፈጥሮ ስፍራ ለጎብኚዎች ምቹ በማድረግ፣ ሎጅና የመሳሰሉት የልማት ስራዎች በመስራት ስፍራዉ በተገቢዉ በማልማት ባለሀብቱ፣ መንግስት እንዲሁም የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል መልዕክታችን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *