በዞኑ በመኸር እርሻ ልማት ከ103 ሺ ሄክታር መሬት በላይ ማልማት መቻሉን ተጠቁሟል
የመምሪያው የማኔጅመንት አካላት በጌታ ወረዳ በሰነንና ቆረፍቻ ቀበሌ በቶዶ መንደር በኩታገጠም በገብስ የለማ ማሳ ጎብኝተዋል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በጌታ ወረዳ በሰነንና ቆረፍቻ ቀበሌ በኩታ ገጠም እየለማ የሚገኝ የገብስ ማሳ ለረጅም ጊዜ በባለሀብት ተይዞ ሳይለማ የቆየ እና በአሲድ የተጠቃ መሬት እንደነበር አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ግብርና ኢንስቲትዩት የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል የባለሙያ፣ የኖራ፣ የምርጥ ዘርና ሌሎችም ድጋፎች ተደርጎ ለምቶ ማሳው በምርጥ ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል።
በዞኑ ከ103 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በመኸር እርሻ በተለያዩ ሰብሎች በማልማት አስፈላጊውን እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከእነዚህም መካከል ከ25 ሺ ሄ/ር በላይ በገብስ መሸፈኑና 17 ሺ ሄክታሩ በኩታ ገጠም መልማቱን ጠቁመው 24 ሺ ሄክታር በጤፍ መልማቱን አንስተዋል።
ከምርምር ማዕከሉ በቅንጅት በተሰራው ስራ የአርሶ አደሩ ውጤታማነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ውጤታማ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የመምሪያው ምክትልና እርሻ ዘርፍ ሀላፊ አቶ አክሊሉ ካሳ በበኩላቸው ከወልቂጤ ምርምር ማእከል በተደረገ የጋራ ጥረት በአሲድ የተጠቁ መሬቶች በማከም ወደ ምርታማነት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
የጌታ ወረዳ ግብርና ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙዘፋ የሱፍ በወረዳው 5ሺ 486 ሄክታር በተለያዩ ሰብል አይነቶች ማልማት መቻሉን ተናግረዋል።
ከዚህም በሰንንና ቆረፍቻ በቶዶ መንደር በ80 ሄክታር መሬት 3 መቶ 28 የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በማደራጀት በገብስ ምርጥ ዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማእከል ከእርሻ ዝግጅት ጊዜ ጀምሮ በሁሉም ዘርፍ ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል።
ማሳው በሚጠበቀው መልኩ በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝም ያነሱት ኃላፊው በሄክታር እስከ 45 ኩንታል ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
በቀበሌው የግብርና ባለሙያ ወይዘሮ ገነት በላቸው እንዳሉት ለአርሶ አደሮቹ ከማሳ ዝግጅት ጊዜ ጀምሮ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙ አንስተዋል።
መሬቱ ከ3 ጊዜ በላይ መታረሱና በኖራ በማከም በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ ማከናወን መቻሉን አንስተዋል።
በኩታ ገጠም እየለማ የሚገኘው የገብስ ማሳ ሲንከባከቡ አግኝተን ካነጋገርቸው ተጠቃሚዎች መካከል ዳንኤል ሙሉጌታ እንዳሉት በማህበር በመደራጀት ማሳው በገብስ መሸፈኑ ጠቅሰው ለማሳው አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረጋቸው ምርቱ በታሰበው ልክ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ምርቱ ወደ ጎተራ እስኪገባ ድረስ ከማሳቸው ሳይነጠሉ እንክብካቤ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።