በአምራቾችና ሸማቾች መካከል ቀጥተኛ ትስስር በመፍጠረር የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋትና በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ የሸማቾች ጥበቃ ሲቪክ ማህበራት ሚናቸው የላቀ መሆኑን የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።


የጉራጌ ዞን የሸማቾች ጥበቃ ሲቪክ ማህበራት ጥምረት የምስረታ ጉባዔ በወልቂጤ ከተማ ተካሄደ፡፡

የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ብርሀኔ እንደገለፁት የፋብሪካና የግብርና ምርቶች ለህብረተሰቡ በብዛትና በጥራት ተደራሽ ለማድረግ የሸማቾች ጥበቃ ሲቪክ ማህበራት የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡

በነጋዴዎችና በሸማቾች መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ ለመስራት የተመሰረተው የጉራጌ ዞን ሸማቾች ጥበቃ ሲቪክ ማህበር ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነፃ በመሆኑ ስራው በነፃነት በመስራት ትክክለኛ የግብይት ስርዓት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡

በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የሸማቾች ጥበቃ የተመሰረተ ሲሆን እንደ ዞን በዛሬው እለት መመስረት ተችሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናና ምክትል ሰብሳቢ፣ ፀሀፊና ሌሎች አባላት ያሉት ቦርድ ተቋቁሟል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ መላኩ ገለፃ እነዚህ የተመረጡ የቦርድ አባላት ሸማቹ የሚመለከቱ ስራዎች በአግባቡ እንዲሰሩ ይደረጋል፡፡

ማህበሩ ከአባላቱ በሚሰበስበው ሀብት የሚተዳደር ለትርፍ ያልተቋቋመ ማህበር ሲሆን በሸማቹ ላይ የሚፈጠሩ የመብት ጥሰቶች ለማስከበር እና ግዴታዉንም ለማሳወቅ በትኩረት እንደሚሰራ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ አቦነህ ወ/ሀዋሪያትና ወርቁ ጋረደው እንደተናገሩት ማህበሩ ከሸማቾች መብትና ግዴታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ይሰራል፡፡

ማህበሩ ለትርፍ የተቋቋመ ሳይሆን በበጎ ፍቃድ ህዝብን ለማገልገል የተቋቋመ በመሆኑ ማንያውም ሰው አባል መሆን ይችላል ብለዋል፡፡

በሸማቾች ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶች ወደ ገበያ እንዳይቀርቡ እና በግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *