የዞኑ አስተዳደር ጽ/ቤት የ2016 በጀት አመት አፈጻጸምና የ2017 ዓመተ ምህረት እቅድ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።
የጉራጌ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ፈቀደ በመድረኩ ላይ እንዳሉት የዜጎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከ2ሺህ 800 በላይ በልማትና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የተነሱ አቤቱታዎችንና ቅሬታዎችን መርምሮ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ ለህብረተሰቡ የሚሰጡ አገልግሎቶች ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
ከህብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በሶስት ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሰራ የገለጹት የአስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊው ይህንንም በመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ ተደራሽነትና ጥራት፣ የቅሬታና አቤቱታ አፈታትና ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት እንዲሁም የሪፎርም ስራዎች ተግባራዊ በማድረግ የዞኑ ጸጥታ በመጠበቅ ሰላም እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ናቸው፡፡
በተገባደደው በጀት ዓመት የመንግስትና የህዝብ አቅም በማስተባበር ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍታት የተቻለ ቢሆንም እያደገ ከመጣው የህዝቡ ፍላጎት አንጻር በተለይም የመብራት አገልግሎት አሰጣጥና የትራንስፎርመር አቅርቦት፣ የኔትወርክ ጥራትና ተደራሽነት፣ የመሬት ጥያቄና ክርክር፣ የድንበር ግጭትና የአምልኮ ቦታ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡
የጉራጌ ዞን አስተዳደር ልዩ አማካሪ አቶ ዳርጌ ተክሉ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በየአካባቢው ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ህብረተሰቡ በማሳተፍ ሊሰራ ይገባል፡፡
የመንገድ ልማት፣ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የመብራት መቆራረጥና የኔት ወርክ ጥራትና ተደራሽነት ላይ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ እንደሚገባ አቶ ዳርጌ አስገንዝበዋል፡፡
የጉራጌ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት የዕቅድ በጀት ዝግጅትና ክትትል የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ እንዳለ አህመድ የአፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ እንተናገሩት የጉራጊኛ ቋንቋ ለማሳደግ በስርዓተ ትምህርት እንዲካተት በጀት ከመመደብ ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ፣ የአረፋና የመስቀል በዓላት በፌስቲቫል ደረጃ በማክበር በመንግስትና በግል የሚዲያ ተቋማት ሽፋን እዲሰጣቸው በማድረግ የጉራጌ ባህል ለማስተዋወቅ አበረታች ስራ ተሰርቷል፡፡
አክለውም የዞኑ የባህል አዳራሽ ግቢ አስፋልት ማንጠፍና የአጥር ግንባታ ስራ፣ ነባሩ የዞን አስተዳደር ህንጻ ጥገናና አዲስ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው ኮምፕሌቅስ የቢሮ ህንጻ በልዩ ሁኔታ ክትትል እየተደረገ እየተሰራ መሆኑን አቶ እንዳለ አብራርቷል፡፡
በዞኑ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ድጋፍ በማጠናከር 5 ሚሊዮን 996 ሺህ 501 ብር የቦንድ ግዢ መፈጸም መቻሉን ጠቁሟል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በአረፋና በመስቀል በዓላት የጉራጌ ህዝብ ባህል በፌስቲቫል ደረጃ በማዘጋጀት በተለያዩ ሚዲያዎች ሽፋን በመስጠት ለማስተዋወቅ የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው ዞኑ የራሱ የሆነ የማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቢኖረው በመደበኛነት የጉራጊኛ ቋንቋ ለማሳደግና ባህሉን በማስተዋወቅ የቱሪዝም መስህብ ማድረግ ይቻላል፡፡
በክረምት ወራት የመሬት መንሸራተት ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች በጥናት በመለየት በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በበጋ ወራት ታቅዶ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም በ2016 በጀት አመት አፈጻጸምና በ2017 በጀት አመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት በማድረግ የጋራ ግንዛቤ የተያዘ ሲሆን በተጠናቀቀው በጀት አመት የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ጽ/ቤቶች የዋንጫና የሰርተፊኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።