በጉራጌ ዞን ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር እየተሰሩ የሚገኙ የግብርና ልማት ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ ኑርዬ ገለጹ፡፡

በዞኑ በመኸር እርሻ እየለማ ካለው ከ103 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በኩታ ገጠም እየለማ መሆኑን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ ኑርዬ እንደገለጹት በጉራጌ ዞን ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር እየተሰሩ የሚገኙ የግብርና ልማት ስራዎች ውጤታማ በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡

በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ አርሶ አደሮች በ420 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም የለማው የጤፍ ማሳ የሰብል ቁመናው አበረታች መሆኑን የገለጹት ዶ/ር መሀመድ ከዚህ ቀደም ሳይታረሱ በመቆየታቸው የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደነበረው ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ መንግስት የግብርናው ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን እንዲረጋገጥ ጥረት ከማድረግ ባሻገር ያልታረሱ መሬቶች እንዳይኖሩ ለአርሶ አደሩ በተፈጠረው ግንዛቤ በተለያዩ አካባቢዎች ሳይታረሱ የቆዩ መሬቶች በማረስ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መንግስት ግብ ጥሎ እየሰራ መሆኑን ዶ/ር መሀመድ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በጉራጌ ዞን በግብርናው ዘርፍ እየታየ ያለው ውጤት ተስፋ ሰጪ በመሆኑ በቀጣይም ሳይታረሱ ያደሩ መሬቶች በማረስ ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው በዞኑ በመኸር ወቅት ከለማው ከ103 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ ከ50ሺህ በላይ ሄክታሩ በኩታገጠም መልማቱንና ምርታማነትን የሚጨምሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ኩታ ገጠም የአመራረት ዘዴ አርሶ አደሮች የኤክስቴንሽን አገልግሎት ለማግኘትና ጉልበታቸውን አስተባብረው ስራቸውን በተቀናጀ መንገድ በመፈጸም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግም ምርጥ ዘር በወቅቱ ከማቅረብ ጀምሮ ለኩታ ገጠም የግብርና ልማት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ ክትትልና ድጋፍ በማድረጋቸው ተስፋ ሰጪ ውጤት መታየቱን ተናግረዋል።

በወረዳው የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ መሀሙድ በወረዳው በመኸር እርሻ ልማት በጤፍ ከለማው 4ሺህ 584 ሄክታር መሬት ውስጥ 2ሺህ 160 በኩታገጠም በማልማት በዚህም 82 ሺህ512 ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።

አርሶ አደሩ በዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የባለሙያ ድጋፍና ክትትል ከማድረግ ባለፈ ግብአት በወቅቱ እንዲያገኙ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።

በቸሃ ወረዳ የውረር በር ቀበሌ አርሶ አደር ሀያቱ ደርብ እንደገለጹት በክላስተር አስተራረስና ሳይታረሱ የቆዩ መሬቶች ማረስ በሚቻልባቸው ዘዴዎች ላይ ግንዛቤ ተፈጥሮላቸው ወደ ተግባር ገብተዋል፡፡

ከሁለት አመት በፊት ሳይታረስ የነበረው መሬት በጤፍ ማልማት ከጀመሩ ወዲህ ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *