ክቡር እንዳሻው ጣሰው በመስክ ምልከታ ወቅት እንደገለፁት ሀገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታስገባቸው የግብርና ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት ከመተካት ባለፈ ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ባለሀብቶች የጀመሯቸው ተግባራት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።
ቴክኖሎጂን በመጠቀም በአነስተኛ ማሳ ከፍተኛ ምርት ማግኘት እንደሚቻል
የአቶ በላይነህ ክንዴና የአቶ ዳኜ ዳባ ማሳ አስረጅ እንደሆነ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው አስገንዝበዋል።
በተለይም በሩዝ ምርት የታየው ውጤታማነት አስደሳች ሲሆን ከክልሉ አልፎ በሀገሪቱ ላይ የሚታየው የሩዝ ፍላጎት ለማሟላት አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለፃ ሀገሪቱ ያላትን ሀብት ተጠቅሞ በማምረት እራስን የመቻል ማረጋገጫ በመሆኑ ተሞክሮው ወደ አርሶ አደሮች ለማስፋት በግብርና ዝመና ላይ ግንዛቤ መፍጠር ይገባል።
ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የምታደርገው ጉዞ ለማፋጠን ግብርናን ማዘመን እንደሚገባ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ሩዝ ከሰፋፊ ማሳዎች አልፎ በአነስተኛ እና በግለሰቦች ማሳ እንዲመረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ከቅባትና ከጥራጥሬ ሰብሎች ባለፈ በፍራፍሬ ሰብል ላይ የታየው ውጤት አበረታች ሲሆን ባለሀብቶቹ ይበልጥ ማምረት እንዲችሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው የመስክ ምልከታው ምርጥ ተሞክሮ ለማስፋት እና ክፍተቶችን ለይቶ ለመፍታት ያስችላል ብለዋል።
ባለሀብቶቹ ያለሟቸው መሬቶች ለዘመናት ሳይታረሱ የቆዩ እንደነበር የተናገሩት አቶ ኡስማን ባለሀብቶቹ መሬቶቹን ተረክበው በአጭር ጊዜ በማልማት አርአያነት ያለው ውጤት ማስገኘት መቻላቸው ገልጸዋል።
በባለሀብቶቹ የለማው የበቆሎ ማሳ በአንድ ሄክታር እስከ 100 ኩንታል ምርት እንደሚገኝ የተናገሩት ኃላፊው የሀገር ውስጥ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር እንደሚቀርፍም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ባለሀብቶቹ ያለሟቸው የአኩሪ አተር፣ የሽንኩርት፣ የሱፍ፣ የስንዴ፣ የበቆሎ ሰብሎች ምርታማነታቸው አበረታች ሲሆን ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻላቸው አስገንዝበዋል።
አክለውም አቶ ኡስማን በዙሪያው ለሚገኙ አርሶአደሮች የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ምርትና ምርታማነታቸውን ማሳደግ ችለዋል ብለዋል።
አቶ በላይነህ ክንዴ እና አቶ ዳኜ ዳባ እንደገለጹት የተረከቡት መሬት በአግባቡ በማልማት ውጤታማ መሆን ችለዋል።
ባለሀብቶቹ ከግብርና ስራቸው ባለፈ የአካባቢው ማህበረሰብ በመንገድ መሰረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ መንገድ መገንባት ችለዋል።
በመስክ ምልከታው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው፣ የክልሉ ዋና የመንግስት ተጠሪ ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ፣ የክልሉ ምክትል ርእሳነ መስተዳድሮች ፣ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ጨምሮ የክልሉ፣ የጉራጌ ዞን እና የእኖር ወረዳ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።