የአዳብና ባህላዊ ጨዋታ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ሶዶ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት አስታወቀ።

የደቡብ ሶዶ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ እስከዳር ሲሳይ እንደገለጹት አዳብና የልጃገረዶችና ወጣቶች ጨዋታ በሶዶ ክስታኔ ቤተ ጉራጌ ማህበረሰብ በድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል።

አዳብና የልጃገረዶችና የወጣቶች ጨዋታ የመተጫጫ ፌስቲቫል ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት 5 በሶዶ ክስታኔ ቤተ-ጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ በድምቀት እንደሚከበር ተገልጿል።

የአዳብና ባህል የልጃገረዶችና የወጣቶች ጨዋታና መተጫጫ ስነስርዓት ሲሆን ባህሉ በጥናት በተረጋገጠው መረጃ መሰረት ከ800 ዓመታት በፊት በሶዶ ክስታኔ ቤተ-ጉራጌ አካባቢ ለዘመናት ሲከበር ኖሯል።

ይህ ባህል በተለያዩ ምክንያቶች ደብዝዞና ሊጠፋ ተቃርቦ የነበረ ሲሆን ከምስራቅ ጉራጌ ባህል ቱሪዝም መምርያ እና የ3ቱ የሶዶ መዋቅሮች እንዲሁም የአዳብና በክስታኔ ዓለም አቀፍ ወጣቶች ማህበር በጋራ በመሆን ባህሉ ጥንታዊ ወጉና ቱባ ባህሉ ይዞ በአሁን ሰዓት በአካባቢው ላይ በፌስቲቫልነት እየተከበረ ይገኛል።

አዳብና በሶዶ ክስታኔ ጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ከጫወታ ባለፈ ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች የሚተጫጩበትና ትዳር የሚመሰርቱበት የወጣቶች ባህል እንደሆነም ነው ወ/ሮ እስከዳር የገለፁት።

ይህም በአካባቢው ዘንድ ትዳር የሚመሰረተው በሁለቱ ተቃራኒ ፆታዎች ምርጫና መፈቃቀድ ብቻ የነበረና የሴቶች መብትና ነፃነት የተጠበቀ መሆኑን ተገልጿል።

ከባህላዊ ጨዋታው በተጨማሪም የተለያዩ ስፖርታዊ ዉድድሮች አጋቲ/ ዝላይ ፣ ሰባ/ ዝላይ እና የተለያዩ የሙየቶች ዝግጅቶችም ለበዓሉ ከፍተኛ ድምቀትም ናቸው ተብሏል።

ወ/ሮ እስከዳር አክለውም ይህ ድንቅ የሆነ የአዳብና ባህል በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በፌሲቲቫልነት እንዲታወቅና በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት በUNESCO እንዲመዘገብ እንዲሁም የቱሪስት መስህብ በመሆን ለአካባቢውና ለአገራችን ኢትዮጵያም የገቢ ምንጭ እንዲሆን አዳብናን የማስተዋወቅ ስራዎች እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

በያዝነው 2017 ዓ.ም አዳብናን ሰፋ ባለና በደመቀ ሁኔታ በፌሲቲቫልነት ለማክበር ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን ዘንድሮ ፌሲቲቫሉ በምስራቅ ጉራጌ ዞን ደቡብ ሶዶ ወረዳ ኬላ ከተማ መስከረም 18 ዞናዊ ፌስቲቫል ይካሄዳል ።

በእለቱም የተለያዩ የክብር እንግዶች የአካባቢው ተወላጆች ይገኛሉ። ስለሆነም ሁሉም አካላት በመገኘት ኩነቱን እንዲከታተልና እንዲሳተፍ ወ/ሮ እስከዳር ጥሪያቸው አቅርበዋል።

ከፌስቲቫሉ በተጨማሪ አዳብና ኬላ ላይ መልከረም 25 እና ጥቅምት 2 : ዳሙ ገነት ላይ መስከረም 22 እና 29 ፣አዴሌ ጨለለቅ መስከረም 21 እና 28 እንዲሁም ደጋ ነረና 23 እና በ30 በተለያዩ ጭፈራዎች ታጅቦ በድምቀት እየተከበረ ዝግጅቱ እስከ ጥቅምት 5 ድረስ የሚቀጥል እንደሆነ ገልፀዋል።

በመጨረሻም ወ/ሮ እስከዳር ለክርስትና እምነት ተከታይዮች በሙሉ እንኳን ለመስቀል በዓል አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል!!!

ዘገባው የደቡብ ሶዶ ወረዳ መንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *