የጉራጌ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ገ/መስቀል ለመላዉ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳቹ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

አቶ አለማየሁ በመልዕክታቸው በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ እጅግ በደመቀ እና በተለየ ስሜት ከሚከበሩ በዓላት ተጠቃሽ በወረሀ መስከረም አጋማሽ ላይ የሚከበረው የመስቀል በአል አንዱ ነው ብለዋል።

የመስቀል በአል የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተለያየ የሚገናኝበት፣ ታላላቆች የሚከበሩበት፣ አዳዲስ ጎጆ የሚቀለስበት፣ በፍቅርና በደስታ የሚከበር በአል ነው።

የመስቀል በአል ከሀይማኖታዊ አስተምህሮቱ ብሎም ውብ ከሆኑ ባህላዊ እሴቶችና ክዋኔዎች ባሻገር የሚያስተምረን በርካታ ቁም ነገር አለው ያሉት አቶ አለማየሁ የዚህም ማሳያ ጌታችን መዳኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል እውነታ ከብዙ ዘመናትና ልፋት በኋላ ከተቀበረበት መገኘቱ ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ አለማየሁ ገለፃ መስቀል በጉራጌ ለበዓሉ ዝግጅት ለወራት ተደክሞበት የሚደሰቱበት፣ በስራውም በደስታውም ሁሉንም ከህፃን እስከ አዋቂ የብሄረሰቡ አባላት በንቃት የሚሳተፉበት፣ የሰው ልጅ ብቻም ሳይሆን የቤት እንስሳትም የሚጠግቡበትና የሚደሰቱበት፣ ሰው ተኮር እሴታችን ጎልቶ ሚታይበት ልዩ በዓል ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ወደ ዞናችን በዓሉን ለማክበር የሚመጡ ተወላጆች እና ጎብኚዎች እንዲሁም በዞኑ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ላይ መሳተፍ፣ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልግ ሁሉ አስፈላጊውን እገዛ የዞኑ መንግስት እንደሚያደረግ ተናግረዋል ።

ህብረተሰቡ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በአሉን ሲያከብሩ ከተቸገሩ ወገኖች ጋር በአብሮነት መሆን እንዳለበት በመግሐጽ በድጋሚ እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *