የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለመስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልእክት አስተላለፉ።

የመስቀል በዓል በጉራጌ ዞን በህዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩ አበይት በዓላት መካከል አንዱ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

የመስቀል በዓል ሀይማኖታዊ ይዘቱ እንዳለ ሆኖ በየአካባቢው እንደየማህበረሰቡ ባህልና ወግም ይከበራል፡፡

የመስቀል በዓል በጉራጌ ከሌሎች ዓውደ ዓመቶች በተለየ በድምቀት በሚከበር በመሆኑ ብዙ ጎብኚዎችን ወደ አካባቢው ይመጣሉ፡፡ በዓሉንም በደስታና በፍቅር አሳልፈው ይመለሳሉ፡፡

የመስቀል በዓል በጉራጌ ብሄረሰብ ሀይማኖታዊ ይዘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ያለው ማህበራዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡

ዓመቱን ሙሉ በስራና በኑሮ ተለያይተው የከረሙ ቤተሰቦችና ዘመዳሞች የሚገናኙበት፣ የከተማና የገጠሩ ማህበረሰብ አንድ ላይ በመሆን ተወያይተው የአካባቢያቸውን ችግሮች የሚፈቱበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ በጋብቻ የተሳሰሩ ቤተሰቦች የሚጠያየቁበት፣ የተጣሉ ሰዎች የሚታረቁበት እና በርካታ ባህላዊ ክንዋኔዎች የሚከናወኑበት ነው፡፡

በሀገር ውስጥና በውጪ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ የጉራጌ ልጆች ወደ ትውልድ ቄያቸው በመትመም በዓሉን ከቤተሰባቸው በማሳለፍ የሚያስደስቱበት፣ የተለያዩ ስጦታዎችና የቤት ቁሳቁስ በማምጣት የሚሰጡበት፣ የእርድ ሰንጋ በሬ በመግዛት በበዓሉ እየተመረቁ ከቤተሰባቸው በደስታ የሚያሳልፉበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዓሉን ከቤተሰባቸው ጋር በማክበራቸው ምርቃትና በረከትን ይቀበላሉ። ምርቃት ለጉረጌ ማህበረሰብ ስንቁ ነው። በበዓሉ ወቅት በአነስተኛ የስራ መስክ ከተሰማሩት ጀምሮ እስከ ትላልቅ ሀብት መፍጠር የቻሉ ባለሀብቶች ድረስ በመስቀል ሀገር ቤት ይከትማሉ።

የጉራጌ ልጆች በህይወት እያሉ ችግር ካልገጠማቸው በቀር የገንዘብ አቅም ማነስ ቢፈታተናቸው እንኳን ተበድረውም ቢሆን ለመስቀል ወደ ወላጆቻቸው ከመሄድ አይቀሩም። ምክንያቱም እናትና አባት፣ ቤተሰብና ጎረቤታቸው በናፍቆት ይጠብቋቸዋል።

የመስቀል በዓል ስናከብር በዓሉ ከሚታወቅበት እሴቶቹ በማጉላት ጥላቻና ቂም-በቀልን በመጠየፍ በፍቅርና በይቅርባይነት ማሸነፍን፣ ትህትና ሆደ-ሰፊነትን፣ ለፍትህ፣ ለእኩልነትና ለእውነት መቆምን ተግባራዊ የምናደርግበት አቅመ ደካሞችና ለተቸገሩ ወጎኖቻችን በዓሉ በደስታ እንዲያሳልፉ ካለን አካፍለን በመስጠትና አብረውን እንዲያሳልፉ በማድረግ ሊሆን እንደሚገባ ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡

ከበዓሉ ጉን ለጎን በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ ሀብቷ የታደለችው ጉራጌ ዞንን በኢንቨስትመንት ተሳታፊ እንዲሆኑና በቱሪዝም ዘርፍ ያሏትን ልዩ ገፀ-በረከቶች እንዲጎበኙ በመጋበዝ
ኑ መስቀልን በጋራ እናክብር በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

    በድጋሚ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የመስቀል በዓል!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *