መስቀል በምስራቅ ጉራጌ ዞን የጉራጌ መስቀል ትውፊቱን የሚያሳይበትና ማህበራዊ መስተጋብሩን የሚያከናውንበት ትልቅ ሃማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በአል በመሆኑ ይበልጥ ማስተዋወቅ እና ማበልጸግ እንደሚገባ ተገለፀ።

የ2017 ዓ.ም የመስቀል በዓል በምስራቅ ጉራጌ ዞን በሶዶ ወረዳ ገነተ ማሪያም ቀበሌ ቱባ ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል ።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊና የባህል ዘርፍ ሀላፊ አቶ ደግነህ ቦጋለ የጉራጌ ብሄረ ሰብ ስራ ወዳድ እና ባህልና ወጉን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚሰራ ፣ በአብሮነትና በአንድነት በመኖር ለሌሎች ፍቅር የሚያሳይ እና እንግዳ ተቀብሎ የሚያስተናግድ ድንቅ ብብሄረ ሰብ ነው ብለዋል።

ብሄረ ሰቡ የመስቀል በዓልን ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ በማክበር የህዝቦች አንደነት እና አብሮነት ደንቅ እሴት ሆኖ እንዲቀጥል እያደረጉ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን በክልሉ በዓይነቱ ለየት ያለ ታሪክ እና ባህል የሚንፀባረቅበት የጥያ መካነ ቅርስ ያለበት የቱሪስት ማዕከል የሆነ ዞን እንደሆነ እና ቅርሱ ለዞኑ፣ለክልሉ እና ለሀገሪቱ ቱሪዝምና ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው ገልፀዋል ።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን መገለጫ የሆኑ የጎርደና ሸንጎ ፣የፈራገዘኘ እና የሲናኖ ባህላዊ ዳኝነት ሰነ ስርዓቶች፣ የብርንዶ፣የጎመን ክትፎ ፣የአዳብና እና አረፋ በዓል ያሉ ባህላዊ እሴቶች፥ የብሄረ ሰቡ ሰላም ወዳድነትና እንግዳ ተቀባይነት ዓርዓያነት ያለው መሆኑ ተናግረዋል ።

በመሆኑም የመስቀል በዓል የጉራጌ ብሄረ ሰብ ትውፊቱን የሚያሳይበትና ማህበራዊ መስተጋብሩን የሚያከናውንበት በመሆኑ ይበልጥ ማስተዋወቅ እና ማበልጸግ እንደሚገባ ተናግረዋል ።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን የመስቀል በዓል ከሀይማኖታዊ እና ከባህላዊ ይዘቱ ባለፈ እጅግ አስደናቂ የሆኑ የፍቅር፥ የአብሮነት፥ የአንድነት ፣የመተሳሰብና የመረዳዳት እሴት የሚታይበት እንዲሁም የጋብቻ ስርዓት የሚፈጸምበት እንደሆነ አስገንዝበዋል።

መስቀልን ጨምሮ ሌሎች የዞኑ ባባህላዊ እና ታሪካዊ ቅርስ በማልማትና ይዘቱን ሳይለቅ ለትውልድ በማስተላለፍ የበለፀገች ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተምሳሌት እናድርጋት ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል ።

የዞኑ ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ብሩክታይት ፀጋዬ የመስቀል በአል በብሄረሰቡ ዘነድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሀማኖታዊና ታሪካዊ ቱፊት ያለው መሆኑን ገልፀው ።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን የበርካታ የቱባው ባህልና እሴት መገኛና የበርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ዞኑ የጉራጌ መነሻ የአይመለልና የጎጎት የቃል ኪዳን ቦታ መገኛና ማራኪ የሆነ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና ድንቅ የሆነ ገፅታ ያላት በበርካታ ፀጋዎች የተሞላች መሆኑን ገልፀዋል።

ማህበረሰቡም ከበዓሉ ጎን ለጎን ተፈጥሮዊ እና ባህላዊ የቱሪስት መዳረሻዎቻችን ማስጎብኘት፣ ማስተዋወቅና ማልማት ይገባዋል ብለዋል ።

የሶዶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ በቴ በወረዳ ከመስቀል በአል በተጨማሪ በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች እንደሚገኙ እና በቀጣይም እነዚህን ቅርሶች በተገቢው ማስተዋወቅ ና ማልማት እንደሚገባ ተናግረዋል።

አክለውም ለአካባቢ የልማትና የየንግድ ስራዎች በስፋት የሚከናወንበት ወጣቶች በአባቶች የሚመረቁበት፣ አብሮነትን የሚንጸባረቅበት መሆኑን ገልጸዋል ።

የበዓሉ ተሳታፊዎችም በአሉ በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ክዋኔዎች የሚፈጸሙበት ሲሆን ማህበረሰቡ የተለመደው አብሮነትን የመቻቻልና የመተሳሰብ ባህሉ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል ።

የብሄረሰቡ መገለጫ የሆኑ እሴቶች፥ ሰላም ወዳድነትና እንግዳ ተቀባይነት ዓርዓያነት ያለው በመሆኑ ለማስተዋወቅና ሌላውም እንዲማርበት ያስችላል ብለዋል።

በመድረኩም ከፌደራል፣ ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳ የተወጣጡ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአካባቢው ተወላጅ ነዋሪዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና ሚዲያዎች ተገኝተዋል።
ዘገባው ጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *