የመስቀል ድባብ አስተጋባ።

➨የመስቀል ድባብ አስተጋባ።

➽እኖር ጋሃራድ ጀፎረ ላይ በሰባተኛው የመስቀል ፌስቲቫል በዓሉን አብስራለች።

(©ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ)
➺➺➺➺➺➺➺➺➺➺➺➺➺➺➺➺➺➺➺

ጋርሃድ ታድሏት። እንዲህ ያለ የኩነት ዓለም፣ ውብ መስክ፣ ንፁህ አደባባይ፣ አስደናቂ ጀፎረ።

እኖር ነኝ። ተረኛዋ ወረዳ ጉራጌን ከየአለበት ሰብስባለች። የምድሩ ሰው ወደ ቀዬው ከመግባቱ በፊት በጋራ በአንድ ስፍራ አንድ ቀን መስቀልን ያከብራል። ያ የመስቀል ፌስቲቫል ይባላል። አረፋንም እንዲሁ በጋራ በተለያየ አካባቢ አድምቀው ያከብሩታል።በዚህ መልኩ መስቀልን በጋራ ማክበሩ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ቆይቶ ሰባተኛው ባለ ተራ እኖር ኾነ። እኔም እኖር ገባሁ። ጋሃራድ ጀፎረ።

ወደ መንደሯ የመጣሁት ቀድሜ ነው።የቀበሌዋ ሰው ልብ ሰፊ ነው። እንደ እናንተ ልመርቃችሁ፤ እልፍ መስቀል ኑሩ።

ዶክተር ጌታቸው ደዊ የጉራጌ ብሔረሰብና የመስቀል በዓል በሚለው ጽሑፋቸው ደመራ ሲደመር “መስቀል ገባ” (መስቀል ገፓም) ተብሎ ስለሚታመን ሁሉም ሰው ይታረቃል፤ መስቀል እርቅ ነውና፡፡ ይላሉ።

በእርግጥም የእርቁ በዓል መስቀል በጉራጌ በደመቀ አብሮነት የሚከበር፣ የሚናፈቅ፣ በእሴት የሚታጀብ ልዩ በዓል ነው።የተቀበለን ቤት እማወራ ወይዘሮ ዘሪቱ ይባላሉ። እውነት ለመናገር እልፍኛቸው ከከተማ ሰፍቶብኝ አልሰለቸኝም። ወይዘሮ ዘሪቱ አብስርን አለማመስገንማ ንፉግነት ነው።

ደጋግማችሁ በመገናኛ ብዙኃን ጀፎረ የጉራጌ አውራ መንገድ ሲባል ሰምታችኋል። ጆሮ አትስጡት። ጀፎረ መንገድ አይደለም። ጉራጌ የጋራ ሀብትን ለመጠበቅ ሥነ ምግባሩን ያፀናበት የእሴት ሰነዱ ነው።

ጀፎረ ለማለፍ በሚል የፀና ቅርስ አይደለም። ጀፎረ የተፈጥሮ መናገሻ ነው። ሰው ከባህል ቃል ኪዳን የገባበት ሰማኒያ ነው። ከጉራጌ ምድር የማይነጠል እንደ ቋንቋው የእሱ መገለጫ እሴት።

ጀፎረ መንገድ ሳይኾን መንገድን ያካተተ አደባባይ ነው። የመንደሮቹ ውበት ከጀፎረው ሞገስ ይቀዳል። ጉራጌ የወል ሀብቱን አይወርም። መሬቱን ባህል ይመትርለታል።ከጥንትም የዥር ዳነ የሚባሉ የቅየሳ ሊቃውንት ነበሩት።ይህ አደባባይ የደስታም የሀዘንም ነው። ሙሽራ በሆታ የሚወጣበት አስክሬን በለቅሶ የሚከበርበት። የልጆች ዓለም፣ የአረጋውያን የትዝታ ጎዳና። የወጣቶቹ የብቃት መንገድ የበቁት ትውልድ የሚሰሩበት ህያው ተቋም። ከስድስት አስርተ ዓመታት በፊት አንድ የጀርመን የቴሌቨዥን ጣቢያ በባህል ሚኒስቴር አማካይነት ወደ ማፌድ መጥቶ ስለ ጀፎረ ዘጋቢ ፊልም መስራቱን አንብቤያለሁ።ይኽው ጋርሃድ ጀፎረ ላይ መስቀል ተበሰረ። ድባቡ ልዩ ነበር። ጉንችሬ ደምቃ ውላለች። ዛሬ የመስቀል ዋዜማ ተቀብሏታል።

አሁን የመስቀል በዓል ድባብ አስተጋብቷል። ወልቂጤ እንዲያውም እንዲያው ናት ይበልጥ ደመቀች። ከጉራጌ ጋር መስቀል ማክበር ብዙ ትርጉም አለው። አሜን ብለው ምርቃት በመቀበል የሚመለሱ እድለኞች ናቸው። እነኚህ ሽማግሌዎች ቀዬውን ይመርቃሉ። ሀገር ሰላም ይሁን ብለው ስለ ምድር ደህና መኾን ከልባቸው ይመኛሉ። የወጣ እንዲገባ ፈጣሪ ከሁላችን ጋር ይሁን ሲሉ ይማፀናሉ። አሜን ፈጣሪ ከሁላችን ጋር ይሁን።

enkssm #Ethiopianhistoryandtourism

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *