ከዞኑ ተቋማት የተደረገላቸው ድጋፍ የነበረባቸውን የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ እጥረት እንደሚቀርፍላቸው እና በርቱው እንደሚማሩ የሞራል ስንቅ እንደሚሆናቸው የወልቂጤ ማረሚያ ተማሪዎች ተናገሩ።

የወልቂጤ ማረሚያ ከጎልማሶች ትምህርት ጀምሮ በምደበኛው ትምህርት ከ1ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ከ300 በላይ የህግ ታራሚ ተማሪዎች በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከማረሚያው የተገኘ መረጃ ይጠቁማል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበራ ወንድሙ በወልቂጤ ማረሚያ ተቋም ተገኝተው ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ሲያስረክቡ ባስተላለፉት መልዕክት በህግ ጥላ ስር መሆን የመጨረሻ ተስፋ የሚቆርጡበት ሳይሆን በስነ ምግባር ታንጸው ትምህርት በመማር እውቀት ሸምተው፣ የፈጠራ ስራና የተለያዩ ሙያዎች ቀስመው እራሳቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል ጠንክረው መማር እንዳለባቸው አደራ ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማርያም በድጋፋ ወቅት እንደገለጹት የ2017 ዓመተ ምህረት ትምህርት በዞኑ በሁሉም አካባቢ መጀመሩን ገልጸው ዛሬ ማረሚያ ተቋም የሚገኘው የታራሚዎች ትምህርት መጀመሩን ለማረጋገጥ እና ታራሚዎች ያለባቸውን የመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ለመቅረፍ ነው።

የህግ ታራሚዎች በቆይታቸው እራሳቸውን የሚቀይሩበት እውቀት ለማግኘት በርትተው መማር እንደሚጠበቅባቸውም ኃላፊው ተናግረዋል።

በወልቂጤ ማረሚያ ተቋም 75 ጎልማችና 321 በመደበኛ ትምህር ከ1ኛ እስከ 10ኛ ክፍል በማስተማር ላይ የሚገኝ ሲሆን በሚቀጥለው አመት እስከ 12ኛ ክፍል ለማሳደግ የመማሪያ ክፍል ግንባታ እያካሄደ መሆኑን ከተቋሙ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው የህግ ታራሚ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሰአዳ ፈይዱ እንዳለችው ዛሬ የተደረገላቸው የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ፣ የንጽህና መጠበቂያ እና ሌሎችም ድጋፎች በትምህርታቸው በርትተው እንዲማሩና የተሻለው ውጤት ለማምጣት የሞራል ስንቅ እንደሚሆናቸው ነው ።
ተማሪ ሳዕዳ በማረሚያው ተቋም ከ7ኛ ክፍል ጀምራ ትምህርቷን እየተከታተለች እንደምትገኝ የግለፀችው ታራሚዋ አሁን ላይ የስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን በተቋሙ እየተከታተለች እንደምትገኝ ተናግራለች።

ተማሪ ካሚል መሐመድ ከ6ኛ ክፍል ጀምሮ ዘንድሮ 10ኛ ክፍል መድረሱን እና የጉራጌ ዞን ውስጥ የሚገኙት ተቋማቶች የመማሪያ ቁሳቁስ እና የተለያዩ ድጋፎች ማድረጋቸው እንዳስደስታው ተናግረዋል።

ተቋማቶቹ ያደረጉት ድጋፍ ጠንክሮ ለመማር እንደሚያስችለው የሚናገረው ታራሚ ካሚል መሀመድ መሰል ድጋፎች በቀጣይ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *