የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማረያም በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ገለጻ የ2017 የትምህርት ዘመን በዞኑ መስከረም 7/ 2017 ትምህርት በይፋ መጀመሩ አስታውቀዋል።

ትምህርት ከመጀመሩ በፊት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን ንቅናቄ የመፍጠር ፣የመማርያ ክፍሎች እድሳት እና ጥገና የማድረግ ፣የመማሪያ ቁሳቁሶች የማሟላት ፣በአጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ዝግጁ የማድረግ ስራዎች መከናወናቸው ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቶች የውስጥ የገቢ አቅማቸው ለማሳደግ እርሻ በማረስ፣ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች የመትከል እና ከብት የማድለብ ስራ እንዲሰሩ መደረጉ አብራርተዋል።

አቶ መብራቴ አክለውም በ2017 በዞኑ ከ1ኛ እስከ 12ኛ ከ2መቶ 34 ሺ በላይ ተማሪዎች ፣ በቅድመ መደበኛ ደግሞ ከ 63 ሺ በላይ ተማሪዎች ለመቀበል ታቅዶ መሰራቱ አመላክተው ከነሀሴ 16 እስከ ጳጉሜ 5 ድረስ ምዝገባ የተደረገ ሲሆን እስካሁን ከ1 መቶ 74 ሺ በላይ ተማሪዎች ተመዝግበዋል።

ይሁን እንጂ እስካሁን መመዝገብ ከነበረባቸው ተማሪዎች ከ55 ሺ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ያልተመዘገቡ በመሆኑ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው ሲሉ አቶ መብራቴ ተናግረዋል።

እንደ ጉራጌ ዞንም የተለያዩ በአላቶች ምክንያት በማድረግ የሚባክኑ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት በመኖራቸው በተለይ “ትምህርት ከመስቀል በኋላ” ነው የሚል ልማዳዊ አመለካከት ጎጂና የተማሪዎች መማርን የሚጎዳ በመሆኑ በአፋጣኝ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ በማድረግ መማር ማስተማሩ ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።

የትምህርት ስርአቱ በክፍለ ጊዜ ፣በደቂቃ ፣በሳምንትና አጠቃላይ በአመት የተሸነሸነ ነው ነገር ግን በርካታ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ባከነ ማለት በትምህርት ውጤት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ቀላል የሚባል እንዳልሆነም አንስተዋል።

እነዚህ የክፍለ ጊዜ ብክነቶች በትምህርት ጥራትና ውጤት አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ በመሆኑ ችግሩን ለማረም የሁሉም ባለ ድርሻ አካል ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በዞኑ አግኝተን ያነጋገርናቸው የጉንችሬ 2ኛ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ንጉሴ ነስሩ እንዳሉት ከዚህ በፊት በትምህርት ቤቱ በተፈጠሩ ተለያዩ ችግሮች ክፍለ ጊዜያቶች ፣በመባከናቸው እና ተማሪዎች ትምህርታቸው በአግባቡ ባለመከታተላቸው የትምህርት ውጤት አሽቆልቁሎ እንደነበር አስታውሰዋል።

ለአብነትም በ2016 አመተ ምህረት የ12ኛ ክፍል ፈተና ከተፈተኑት ምንም እንዳላሰላፈ ጠቁመው በዘንድሮ አመት ግን 30 ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲ ማስገባት መቻሉ ተናግረዋል።
ይህ የሆነው ተማሪዎች በወቅቱ በትምህርት ገበታቸው በመገኘታቸው ፣የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመሰራታቸው ፣የትምህርት ግብአቶች በመሟላታቸው ሲሆን በ2017 ይህንን በማጠናከር ለበለጠ ውጤት እንሰራለን ሲሊ መምህር ንጉሴ ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *