መስቀል በጉራጌ” የንግድ ትርኢት ኤግዚብሽንና ባዛር በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ተከፈተ።

በዞኑ ወልቂጤ ከተማ የተከፈተው የንግድ ትርኢትና ባዛር የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃና ገጽታዋ እንዲጎላ ከማድረግ ባለፈ የህብረተሰቡን እሴት በማስተዋወቅ ረገድ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገለጸ።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንዳሉት የንግድ ትርኢትና ባዛር መዘጋጀቱ የከተማው የንግድ እንቅስቃሴ ከማሳለጥ ባለፈ የህብረተሰቡን ባህልና እሴት በማስተዋወቅ ረገድ ፋይዳው ትልቅ ነው።

በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ባዛርና ኤግዚብሽን የሚዘጋጅ መሆኑን ያነሱት አስተዳዳሪው በከተማዋ የተዘጋጀው የንግት ትርኢትና ባዛር በጥራት፣ በመጠንና በዋጋ ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የንግድ ትርኢትና ባዛሩ በሰላማዊ መንገድ እስኪጠናቀቅ ድረስ የዞኑ አስተዳደር አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ አቶ አበራ ገልጸዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው በበኩላቸው የንግድ ትርኢትና ባዛሩ አላማ በከተማው ያለው ኢንቨስትመንት ለማነቃቃት፣ ሰላም፣ ስራ ወዳድና ትጉህ ማህበረሰብ ያለባት ከተማ መሆናን ለማሳየት ያለመ ነው።

ከዚህም ባለፈ በንግዱ ማህበረሰብና በሸማቹ ማህበረሰብ ያለውን ግንኙነት ጠንካራ መሰረት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ተግባሩ እንዲሳካ ላደረጉ ለዞንና ከተማ አስተዳደር የንግድና ገበያ ልማትና ለባህል ቱሪዝም ተቋማት እንዲሁም ለአዲና ፕሮሞሽንና ለሎችም ምስጋና አቅርበዋል።

የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ብርሃኔ እንደገለጹት መስቀል በጉራጌ በሚል የተዘጋጀው የንግድ ትርኢትና ባዛር የኑሮ ውድነቱ ከማረጋጋት ጎን ለጎን የማህበረሰቡን እሴት እንዲተዋወቅ ሚናው ከፍተኛ ነው።

የባዛሩ መዘጋጀት ማህበረሰቡ የሚፈልጋቸው እቃዎች በአንድ ማዕከል እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር በዋጋ ደረጃ ቅናሽ እንዳለው አቶ መላኩ አንስተዋል።

በዚህም የዋጋ ግሽበቱ በሚያረጋጋ መልኩ የፍጆታ እቃዎች፣ የተማሪዎች ቁሳቁስና ሌሎችም በርካታ እቃዎች እንዲገቡ መደረጉን ገልጸው ህብረተሰቡ ባዛርና ኤግዚብሽን ገብተው እንዲሸምቱም ጥሪ አቅርበዋል።

መምሪያው የበዓል ወቅት እንደ መሆኑ መጠን ስግብግብ ነጋዴዎችን ላይ ቁጥጥር ከማድረግ ባለፈ ጊዜ ያለፈባቸውና ከባዕድ ጋር የተቀላቀሉ ነገሮች እንዳይኖሩ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የከተማው ምክትል ከንቲባና ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙባረክ ዘይኑ በከተማው የባዛሩ መከፈት ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባለፈ የከተማዋ ገጽታ በማጉላት ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው።

አክለውም የንግዱ ፍትሃዊነት በሚያረጋግጥ መልኩ በከተማው የማይገኙ ቁሳቁሶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙና የንግድና የኢንቨስትመንት ስራዎችን እንዲነቃቃ ያደርጋል ብለዋል።

በንግድ ባዛርና ኤግዚብሽኑ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን ይህም ማህበራዊ ትስስርና መስተጋብሩን የበለጠ እንደሚያሳልጥ ገልጸዋል።

የአዶት የጉራጌ ዞን የነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ሮዛ አግዛ ማህበሩ በነጋዴው ማህበረሰብን እና በመንግስት መካከል እንደ ድልድይ በመሆን በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለውን ህገወጥ ንግድ፣ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት፣ ከካፒታል በላይ ክምችቶችን በተቀናጀ መንገድ በመግታት ጉልህ አበርክቶ ያደርጋል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *