በዞኑ በኢንቨስትመንት በሁሉም ዘርፍ ያሉ አማራጮችን በተገቢው በመጠቀም ውጤታማ ስራ ለመስራት በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን መፍታት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ገለጸ።

መምሪያው በ2016 ዓ.ም የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ የአፈጻጸም ግምገማ ግብረ መልስ፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ሌሎችም ላይ ከወረዳው አመራሮች ጋር ውይይት አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ አመተሩፍ ሁሴን እንዳሉት በዞኑ በሁሉም ዘርፍ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች በተገቢው በመጠቀም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት ይገባል።

በዞኑ በዘርፉ የተሻለ ስራ የሚሰሩ የኢንቨስትመንቶች ተሞክሮ ማስፋት ይገባል ያሉት ኃላፊዋ ፍቃድ ወስደው አጥረው ባስቀመጡና ለሌላ አላማ በሚያውሉ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

አክለውም ፍቃድ ወስደው ወደ ተግባር የሚገቡ ኢንቨስትመንቶች ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በዞኑ በግብርና 136፣ በኢንቨስትመንት 118 እና በአገልግሎት ዘርፍ 61 በአጠቃላይ 315 ኢንቨስትመንቶች ፍቃድ ወስደው ወደ ተግባር እንደገቡም አመላክተዋል።

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ በዘርፉ ያሉ ማነቆዎች ለመፍታትና ውጤታማ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአበሽጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሱ ጁሀር በበኩላቸው በወረዳው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ለዚህም በዘርፉ ውጤታማ ስራ በመስራት ዞኑ ብሎም ወረዳው ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ነው ያሉት።

መምሪያው በዘርፉ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች አበረታች መሆኑን ያነሱት አስተዳዳሪው ተግባሩ በቀጣይ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት በዞኑ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢንቨስትመንት ዘርፍ ውጤታማ ስራ ለመስራት በዘርፉ ላይ ያሉ ማነቆዎችን መፍታት እንዳለባቸውም አመላክተዋል።

ከዚህ ቀደም ፍቃድ ወስደው ወደ ተግባር ያልገቡ ኢንቨስትመንቶችና ከወሰዱበት አላማ ውጪ በሚጠቀሙት ላይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም አንስተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *