በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፉን ማጠናከር እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ አስታወቀ።


መምሪያው የ2016 አፈጻጸም ግምገማና የ2017 ዓ.ም እቅድ ላይ አመታዊ ጉባኤው በወልቂጤ ከተማ እካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ በዚህ ወቅት በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፉን ማጠናከር ግድ ይላል ብለዋል።

በመሆኑም የፈጠራና ኢኖቬሽን ተግባራቶች ማጠናከር ፣በት/ቤቶች ሞዴል የሆኑ ክበባቶች መፍጠር፣በሁሉም ወረዳዎች ዌብ ሳይቶች ማበልጸግ፣ ለዘርፉ የሰው ሀይል ፣በቂ የሆነ በጀት ፣ቁሳቁስ እና በአጠቃላይ ልዩ ትኩረት ከተሰጠው ሀገራችን በቴክኖሎጂ መቀየር እንደሚቻል አስረድተዋል።

ለዚህም ተቋማት በተለይ ኮሌጆች ፣የትምህርት መዋቅር ፣ዩኒቨርስቲ እና ከሚመለከታቸው ሴክተር ተቋማቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር መቀናጀት ያስፈልጋል ብለዋል አቶ ደምስ ገብሬ።

በህብረተሰቡ የዲጂታላይዜሽን አስተሳሰብ እንዲሰርጽ ለ1ሺ 6 መቶ 11 በመሰረታዊ የኮምፒውተር ስልጠናና ከ46 በላይ ለሚሆኑ ባለሙያዎች የአድቫንስ ስልጠና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን መሰጠቱ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን አስተዳደር ልዩ አማካሪ አቶ ዳርጌ ተክሉ እንደገለፁት በማህበረሰቡ ዘንድ የቴክኖሎጂ ስርጸት እንዲኖር የግንዛቤ ስራዎችን መስራት እንዲሁም በእጃችን ያሉ ቁሳቁሶችንና የተመቻቹ የቴክኖሎጂ እድሎች በአግባቡ ልንጠቀምባቸው ይገባል ነው ያሉት።

በመሆኑም በቅርቡ እንደሀገር የተመቻቸው የኮደሮች ስልጠና ሁሉም ሰው የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ዳርጌ ከኔት ወርክ ተደራሽነት እና መቆራረጥ ጋር የሚታየው መስተጓጎል ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ የሰጠዋል ብለዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ አካላት በበኩላቸው ዘመኑን የተደረሰበት ደረጃ ለመድረስ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፉን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

በዘርፉ በተለይ የበጀት ፣የቁሳቁስና የሰው ሀይል እጥረት እንዳለ የጠቆሙት ሀሳብ ሰጪዎቹ እነዚህ ጉድለቶች በማረም በአመቱ የታዩ አበረታች ለውጦች ይበልጥ ለማጠናከር ከተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መስራት ይገባል ብለዋል።

በቀጣይ እንደሀገር እየተሰራበት ያለው የኢኮደር ተግባር ስራ አጠናክሮ በመስራት እና በአመቱ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ በማስቀጠል ጉደለቶች ደግሞ በማረም በዘርፉ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በእለቱም የ2017 እቅድ ከሚመለከታቸው ሴክተር ቋማት ፣ከወረዳዎችና ከከተማ አስተዳደሮች የግብ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ባለሙያዎችና መዋቅሮች እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በዚህም ከወረዳዎች 1ኛ እዣ ወረ፣ 2ኛ ምሁር አክሊል ወረዳና 3 እኖር ወረዳ ሲሆኑ ከከተማ አስተዳደሮች ደግሞ ወልቂጤ ከተማ 1ኛ ወጥቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *