ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ህገወጥነትን በመከላከል ከመንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው አሳሰቡ።


በከተማው በተጠናቀቀው በጀት አመት 1 መቶ 67 ሄክታር መሬት ማስመለስ መቻሉን ተጠቆመ።

የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው እንዳለት ከዚህ በፊት የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን በማስተካከል በተለይም የህዝብና የመንግስት መሬቶች ለህዝብ አገልግሎት ብቻ እንዲዉሉ ከፍትህ ተቋም ጋር በመሆን የህዝብና የመንግስትን ጥቅም ማስከበር ተችሏል።

በከተማው የመንግስት መሬት በህገወጥ አካላት ቁጥጥር ስር በመውደቁ መንግስት የራሱን ጥቅም እያጣ እንደነበረ ያነሱት ከንቲባው ባለፈው አመት 1 መቶ 67 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ማስገባት መቻሉና ይህም በገንዘብ ሲተመን 300 ሚሊየን ብር ሀብት ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።

የከተማው መንግስት ስራው ውጤታማ እንዲሆን አቃቢ ህግና የፍትህ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ መደረጉን ገልጸው በመሬት ነክ ጉዳዮች ከተያዙት 29 መዝገቦች ሀያ ሶስቱ የከተማው መንግስት የረታባቸው ሲሆን ሁለቱ የተረታባቸውና 4ቱ በይግባኝ ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።

ከተማዋን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ህገወጥነትን መከላከል እንደሚገባ ጠቁመው ለዚህም ህብረተሰቡ ህገወጥነትን በመጠየፍ በልማት፣ በሰላምና በመልካም አስተዳደር ተግባራት ከመንግስት ጎን በመሰለፍ እገዛ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በተጠናቀቀው በጀት አመት የመንግስትና የህዝብን ሀብት ከምዝበራ ለመታደግ በተሰራው ስራ ለመጣው ውጤት የዞኑ፣ የከተማው የመንግስት አካላትና ህብረተሰቡ ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የወልቂጤ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ ይብጌታ ንጋ በበኩላቸው ባለፈው በጀት አመት በከተማው የህዝብና የመንግስት ሀብት ለማዳን ከፍትህ ተቋማት ጋር በመሆን ቤት፣ገንዘብና የኦዲት ግኝቶችን ማስመለስ ተችላል ብለዋል።

ለዚህም ውጤታማነት ሁሉም በቅንጅት በተሰራው ስራ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ተግባሩ አጠናክሮ ለማስቀጠል ህብረተሰቡ አገዛ እንዲያደርጉ ጠቁመዋል።

የወልቂጤ ከተማ ፍትህ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ ዳግየ እንደገለጹት በተቋሙ የሪፎርምና ለዘርፉ ብቁ ባለሙያ በመመደብና በመቀናጀት የመንግስት ንብረቶች በማስመለስ ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ እምነት እንዲኖረው ተደርጓል።

በዚህም ከወልቂጤ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እስከ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመሄድና የህገ መንግስት ትርጓሜ ድረስ በመጓዝ የመንግስት ሀብት ማስመለስ መቻሉን አንስተዋል።

ተግባሩ እንዲሳካና ውጤታማ እንዲሆን ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *