መጪው የሚከበሩ በዓላቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መደረጉ የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ።


የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ እና የዞኑ ፖሊስ መምሪያ በጋራ በመሆን የዘመን መለወጫ እና የመስቀል በዓላቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ በማስመልከት ከጸጥታ አካላት ጋር በወልቂጤ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ የህያ ሱልጣን በዚህ ወቅት እንዳሉት ከጊዜ ወደ ጊዜ በዞኑ በተለይ በወልቂጤ ከተማ ጸጉረ ልውጦች እየተበራከቱ በመሆኑ ህብረተሰቡና የጸጥታ አካላት ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አያይዘውም በዞኑ ሰላምን ለማምጣት በተደረጉ የጋራ ስራዎች ውጤት ማምጣት መቻሉ የገለጹት አቶ የህያ ቢሆንም አሁንም አንድ አንድ አካባቢዎች ላይ የጸጥታ ችግሮች እየተበራከቱ በመሆኑ የጸጥታ አካሉ ነባራዊ ሁኔታን ማጤንና በቂ ዝግጅት እንዲያደርግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

አክለውም በጽንፈኝነት ተግባር የነበሩ አካላት ፣ህገ ወጥ የጦር መሳረያዎች፣ቦምብ እና ሌሎችም በቅርቡ በቁጥጥር መዋላቸው አስታውሰዋል።

እንደ አቶ የህያ ገለጻ መንገድ የሚዘጉ፣ህግና ደንብ በማያከብሩ፣ለግል ጥቅምና ፖለቲካ በሚንቀሳቀሱ ፣የህብረተሰቡ አንድነትና ሰላምን የሚያናጉ አካላት በህግ አግባብ ማዋል ያስፈልጋል ብለዋል።

በአድ ነገር ቀላቅሎ መሸጥ፣ያላግባብ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ፣ ሀሰተኛ ገንዘቦችን ማዘዋወር፣አካባቢን ማወክ፣ስርቆቶችንም ጭምር ስለሚበራከቱ ትኩረት ይሻሉ ብለዋል ኃላፊው።

የአካባቢ ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ ማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ስራ ማጠናከርና በተለይ ህብረተሰቡና የጸጥታ አካሉ ጥብቅ ትስስር ሊኖር እንደሚገባ አቶ የህያ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ገና ደገሙ እንዳሉት መጪው በአላቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ እና የዞኑ ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከርና ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ማድረግ፣ዘርፉን በቂ የሰው ሀይል ማሰማራት ይገባል።

አክለውም ወረዳ ከወረዳ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸው ዞኑ ከአጎራባች ዞኖች ጋር በጋራ ለመስራት ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

በትራንስፖርት ዘርፍ፣በሆቴሎች ፣በሺሻ ቤቶች ፣አልጋ ቤቶች እና ህገ ወጥ መሳረያ እንዳለባቸው በሚጠረጠሩ አካባቢዎች ድንገታዊ ፍተሻዎች እንዲደረጉ ኢንስፔክተር ገና ደገሙ መመረያ ሰጥተዋል።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ ምክትልና የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ግሩም ወ/ሰንበት በበዓላት ወቅት ሰላማዊ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር በትኩረት እየተሰራበት እንደሆነ ተናግረዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የጸጥታ አካላት እንደገለጹት ከዚህ በፊት የነበሩ ጠንካራ የጸጥታ ስራዎች ልምድ በመጠቀም እና ቅንጅታዊ አሰራሮች በማጠናከር በዓላቶቹ በሰላም እንዲጠናቀቁ የበለጠ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

የዞኑ ሰላምና ጸጥታ በማረጋገጥ በአሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ፣የጸጥታ አካሉ እና ሚመለከተው ሁሉ ተቀናጅቶ መስራት እንዳለበት ሀሳብ ሰጪዎቹ አስታውቀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *