ጳጉሜን 5 የነገ ቀን ምክንያት በማድረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አንደኛ አመት ምስረታ በዓል “በአዲስ ምዕራፍ በወል እሴት ወደ መስፈንጠር” በሚል መሪ ቃል በጉራጌ ዞን በተለያዩ ዝግጅቶች በወልቂጤ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑሪዬ በበዓሉ ተገኝተው እንዳሉት ከክልሉ ምስረታ ጋር ተያይዞ የነበረው የሰላም፣ ጸጥታ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ከህዝቡ ጋር በርካታ ውይይቶች በማካሄድ እና ግንዛቤ በመፍጠር አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ተችሏል።

ይህም አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ የክልሉ መንግስት የ100 ቀናት እቅድ በማቀድ በሁሉም ዘርፍ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አመላክተዋል።

በዞኑ ወልቂጤ ከተማ፣ አበሽጌ ወረዳና ቆሴ ከተማ እየተስተዋሉ ያሉ የሰላምና ጸጥታ ችግሮች ለመፍታት የክልሉ መንግስት እንደሚሰራ የገለጹት ዶክተር መሀመድ ኑሪዬ በዚህም ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል ብለዋል።

ክልሉ በ2017 በጀት አመት በሁሉም ዘርፍ ያሉ ጸጋዎችን በተገቢው በመለየት የበለጠ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመስራት ባለፈ የወል እሴት በመገንባት የክልሉ ህዝቦች አንድነትና አብሮነት ለማጎልበት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳደር አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት ክልሉ ከተደራጀ አንድ አመት ቢሆንም በሁሉም መስኮች ውጤታማ ተግባራት ማከናወን መቻሉና በዚህም የጉራጌ ዞን የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱ ጠቅሰው ተግባሩ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።

በዞኑ ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ አለመረጋጋት በማረም አንጻራዊ ሰላም ማምጣት መቻሉን ያነሱት አቶ ላጫ በተጠናቀቀው በጀት አመት ህብረተሰቡን ከመንግስት ጎን በማሰለፍ በሁሉም ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት ዞኑ በክልሉ ብሎም በሀገር ደረጃ ተሞክሮ መቀመሪያ ማዕከል ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።

በዞኑ የተመዘገበው ውጤቶች በቀጣይ ይበልጥ በማስቀጠል የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት በዞኑ ውስጥ በተለይም በወልቂጤ ከተማ፣ በአበሽጌ ወረዳና በቆሴ ከተማ አካባቢ እየተስተዋሉ ያሉ የሰላምና ጸጥታ ችግሮች ለመፍታት ከክልሉ መንግስት በመቀናጀት እንደሚሰራ አንስተዋል።

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እንደስሙ የሁሉ ነገር ማዕከል እንዲሆን በሚደረገው ጥረት የዞኑ ህዝብ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወት አቶ ላጫ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል በበኩላቸው እንደ ሀገር ያለው የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በዞኑ በግብርናው ዘርፍ በትኩረት ከመስራት ባለፈ ህገወጥ ነጋዴዎችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ማገዝ ይኖርበታል።

ወልቂጤ ከተማ ስማርት ሲቲ ለማድረግ እንደሚሰራ ያነሱት አቶ አለማየሁ በዚህም የህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዳሉት በክልሉ ብሎም በዞኑ እየተመዘገቡ ያሉ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በዞኑ ወልቂጤ ከተማ፣ አበሽጌ ወረዳና ቆሴ ከተማ ላይ እየተስተዋሉ ያሉ የሰላምና ጸጥታ ችግሮች የክልሉ መንግስት በቁርጠኝነት ሊፈታ ይገባል።

የክልሉ ህዝቦች አንድነትና አብሮነት ይበልጥ እንዲጎለብት ማድረግ፣ወልቂጤ ከተማ ስማርት ሲቲ ለማድረግ መስራት፣ የኑሮ ውድነት ማረጋጋትና ሌሎችንም አንስተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *