የጉራጌ ዞን አብይና ቴክኒክ ኮሚቴ ከወረዳና ከከተማ አስተዳደር አብይና ቴክኒክ ኮሚቴዎች ጋር እንደ ሀገር በሚሰጠው የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ዙሪያ በዙም ሚቲንግ ውይይት አካሂዷል።

በዞኑ ለ37 ሺህ 5 መቶ 3 የህብረተሰብ ክፍሎች የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና እንደሚሰጥ የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ገለፀ ።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንዳሉት እንደ ሀገር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢንሼቲቭ 5 ሚሊዮን ወጣቶች የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ይሰጣል።

ወቅቱ የቴክኖሎጂ ዘመን እንደመሆኑ መጠን በዞኑ በሁሉም ደረጃ ብቁ በገበያ ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ሁሉም በቅንጅት መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ለዚህም ሁሉም በዞኑ የሚገኙ ሰልጣኞች በተገቢው ተመዝግበው ስልጠናው ተከታትለው መጨረስ እንዳለባቸው አቶ አበራ አመላክተዋል።

የዞኑ ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆንና ተግባሩ ውጤታማ እንዲሆን የዞኑ አብይና ቴክኒክ ኮሚቴ ተግባሩ በመገምገም በትኩረት ስራዎች እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ስልጠና በሚሰጥባቸው ማዕከላት የመብራትና የኢንተርኔት መቆራረጥና አቅም ማነስ ችግሮችን ለመፍታት መብራት ሀይልና ኢትዮ ቴሌኮም በትኩረት መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ በበኩላቸው የኢትዮ- ኮደርስ ኢንሼቲቭ በዞኑ 37 ሺህ 5 መቶ 3 ሰልጣኞች በሶስት አመታት ስልጠናው የሚሰጥ ሲሆን በዘንድሮ አመት የዞኑ ማዕከል ጨምሮ በ15ቱም መዋቅሮች ለ9ሺህ 9መቶ 86 የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠናው ለመስጠት ታቅዷል።

ስልጠናው ለስድስት ሳምንታት በዩኒቨርሲቲ፣ በኮሌጆች፣ የተሻለ ግብአት ባለባቸው ትምህርት ቤቶች ስልጠናው ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ኃላፊው ጠቅሰው ለዚህም ለዞኑ ሲቪል ሰርቫንት ተገቢውን ግንዛቤ በመፍጠር ምዝገባ ተጀምሯል ነው ያሉት።

የስልጠናው አላማ ሀገሪቷ በ2025 ዲጂታል ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው ለሰልጣኞች የስራ ዕድል ፈጠራ የሚፈጥር እንደሆነም አንስተዋል።

ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ለተግባሩ ትኩረት በመስጠት መስራት እንዳለበት አንስተው ሰልጣኞችም ስልጠናው በተገቢው ተከታትለው በመፈተን ሰርተፍኬት ከማግኘት ባለፈ የተሻለ ውጤት ለሚያመጡ ሰልጣኞች ለተሻለ ስልጠና ስፖንሰር እንደሚደረጉም ተናግረዋል።

የዙም ሚቲንግ የውይይት ተሳታፊዎች እንዳሉት ስልጠናው ብቁ ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው በተግባሩ ወቅት የመብራት መቆራረጥና የኢንተርኔት አቅም ማነስ እንዳይገጥም እንደስጋት አንስተዋል።

ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት በዘርፉ ያሉ ማነቆዎች እንዲፈቱ በቅንጅት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *