እንደ ሀገር ያሉ እምቅ አቅሞችን አቀናጅቶ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ ሁሉም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ማሞ ገለጹ።


በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉአላዊነትና ክብር” በሚል መሪ ሀሳብ ሕዝባዊ የዉይይት መድረክ ተካሂዷል።

በህዝባዊ የውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ማሞ እንዳሉት ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ብትሆንም ለበርካታ አመታት በተረጂነት መኖሯን ገልጸው ያላትን እምቅ ጸጋዎች በተገቢው በመጠቀም ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ ሁሉም ርብርብ ማድረግ ይገባል።

እንደ ሀገር ምርታማነት ለማሳደግ የግብአት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ መንግስት በርካታ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ የገለጸት አቶ ጸጋዬ ማዳበሪያው ለአርሶ አደሩ በፍትሃዊነት እንዳይደርስ የሚያደርጉ ህገወጦች ከተግባራቸው ሊታረሙ ይገባል ነው ያሉት።

ወጣቶች በግብርናው ዘርፍ የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የታቀደው እቅድ ከግብ እንዲደርስ በዘርፉ በማደራጀት በትኩረት እንዲሰራም ተናግረዋል።

በዞኑ በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸው ይህም በቀጣይም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመላክተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ ኑሪዬ በበኩላቸው እንደ ሀገር ከተረጂነት ለመላቀቅ የማህበረሰቡ የአስተሳሰብና የአመለካከት ችግር ለመቅረፍ በትኩረት መስራት ይገባል።

እንደ ሀገር በማህበረሰቡ ዘንድ ልመናና ተረጂነት አጸያፊ ተግባር መሆኑን ያነሱት አቶ መሀመድ ሀገር በቀል የመረዳዳት ባህል በመጠቀም በራስ አቅም በማምረት ከተመጽዋችነት መላቀቅ ይኖርብናል ብለዋል።

ከተረጂነት ለመላቀቅ የመሰረተ ልማት የተደራሽነትና የጥራት ችግሮች መኖሩን ገልጸው በክልሉ የተጀማመሩ መሰረተ ልማቶች ለማጠናከር መንግስትና የህብረተሰቡ ተሳትፎ በማጠናከር እንደሚሰራ ጠቁመው ለዚህም የጉራጌ ማህበረሰብ ከመንግስት ጋር በመቀናጀት እየሰራ ያለው ስራ አድንቀዋል።

ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው ያሉት ዶ/ር መሀመድ በዞኑ የነበረው የሰላምና የጸጥታ ችግር የህብረተሰቡ የቆየ እሴት በመጠቀም በተሰራው ስራ የተሻለ ለውጥ መምጣቱን ተናግረው ለዚህም የክልሉ መንግስት የዜጎች ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደገለጹት የሀገር ሉአላዊነት ለማስከበርና ከተረጂነት ለመላቀቅ ያሉ እምቅ አቅሞችን በማቀናጀት መስራት ይኖርብናል።

ታታሪ እና ስራ የማይንቅ ህዝብ ይዘን ለተረጂነት ተጋላጭ መሆን የለብንም ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በዞኑ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ማህበረሰቡ በማሳተፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የዞኑ ማህበረሰቡ ከመንግስት ተቀናጅቶ በርካታ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ያነሱት አስተዳዳሪው መንግስት ማህበረሰቡን በማሳተፍ 235 ኪሜ መንገድ በህዝብ ተሳትፎ መገንባቱን ገልጸው በቀጣይ አመት ሁሉም የገጠር ቀበሌዎች በመንገድ በማገናኘት ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።

በዞኑ ምርታማነትን ለማሳደግ ሁሉም መሬቶች እንዲታረሱ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በተያዘው በጀት አመት በዞኑ ከዚህ ቀደም ታርሰው የማያውቁ ከ4ሺ ሄ/ር በላይ መሬት በማረስ ወደ ልማት ማስገባት ተችላል ነው ያሉት።

በዞኑ እየተስተዋለ ያለው ህገወጥ የመሬት ወረራ፣ ደላሎች፣ የመሳሪያ ዝውውርና ኮንትሮባንድ ላይ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ የገለጹት አስተዳዳሪው ህገወጥነት ለመከላከል ከክልልና ከፌደራል መንግስት በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነም አመላክተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት በዞኑ በልማትና በመልካም አስተዳደር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆኑን ገልጸው እነዚህን በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥሉ ይገባል።

የጉራጌ ማህበረሰብ ተረጂነትና ልመና አብዝቶ የሚጠየፈው ተግባር መሆኑ ያነሱት ተሳታፊዎቹ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት በትኩረት ተግተው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

ሀገሪቷ ብሎም ዞኑ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች መኖሩን ገልጸው ከተረጂነት ለመላቀቅ ያሉ የመሬት፣ ውሃና የሰው ሀይል ሀብቶቻችን በተገቢው በማቀናጀት በትኩረት መስራት ይገባል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *