በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም በማምረት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ ክልላዊ የቡናና የሮዝመሪ ችግኝ ተከላና የበቆሎ፣ የቡናና የሮዝመሪ ማሳ ጉብኝት ተካሂዷል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሪዱዋን ከድር በመስክ ምልከታ ላይ እንዳሉት በክልሉ 147 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በቡና ተክል መሸፈን የተቻለ ሲሆን በተያዘው በጀት አመት የቡና ተከላ ሲጠናቀቅ 153 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና ተክል ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ አይነት ቅመማ ቅመም ለማምረት ምቹ የአየር ንብረት መኖሩን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በክልሉ ሮዝመሪ ከ10 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ እንዲሁም በርበሬና ዝንጅብል በማምረት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆን ችሏል፡፡

በዚህም በርበሬና ሮዝመሪ ወደ ወጭ ሀገር በመላክ ከ11 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን አቶ ሪዱዋን ተናግረዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በፕሮግራሙ ላይ እንዳሉት በክልሉ ቡና በከፍተኛ መጠን ከሚመረትባቸው አካባቢዎቸ አንዱ የጉራጌ ዞን ሲሆን ከ48 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በቡና ተክል መሸፈን መቻሉንና በየዓመቱም ከ2 እስከ 3 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ተጨማሪ በመትከል እድገት እያሳየ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የሚታወቀው ሮዝመሪ አርሶ አደሩ በማምረት ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ለእርሻ ልማት ሊውል የሚችል ሰፊና ለም መሬት በባህር ዛፍ መወረሩን የገለጹት አቶ ላጫ በእኖር ወረዳ ሞዴል አርሶ አደሮች ባህርዛፍ በመንቀል ቡናና ሙዝ በመትከል ላይ መሆናቸው በተካሄደው የመስክ ምልከታ አረጋግጠው ይህንን ተግባር በሁሉም አካባቢ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

በዞኑ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአረንጓዴ ልማት ስራ የምግብ ዋስትና ሊያረጋግጡ የሚችሉ ፍራፍሬዎች በመትከል ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም 48 ነጥብ 3 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ቡና የሚለማ ሲሆን በዘንድሮ አመት 4 ሺህ 627 ሄክታር መሬት ላይ 14 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ አዲስ የቡና ችግኝ ለመትከል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

ዞኑ ለቡና ልማት ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት ያለው በመሆኑ ምክንያት ቡና በስፋት የሚያመርቱ ምዴል አርሶ አደሮችና መንደሮች ተፈጥሯል ያሉት አቶ አበራ ከዚህ ጎን ለጎን 30-40-30 የፍራፍሬ ልማት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የእኖር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቱ ትክሌ በመስኩ ላይ እንደገለጹት በወረዳው ከ14 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በቡና በመሸፈን የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እጨመረ መጥቷል፡፡

በዚህም በየዓመቱ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች በመትከል 1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ተጨማሪ የቡና ማሳ የማሳደግ ስራ በቀጣይነት እየተሰራ እንደሚገኝ ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡

አቶ ካሚል ሽፋ በእኖር ወረዳ በካሳይ ቀበሌ የሚገኝ ሞዴል አርሶ አደር ሲሆን የቡና ችግኝ ተከላና የቡና ማሳ የመስክ ምልከታ በሚኬድበት ወቅት እንደተናገረው በ2 ሺህ 2 ሄክታር መሬት ላይ ቡናና ሙዝ በማምረት ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም በጓሮ የሚገኝ ባህርዛፍ በማስወገድ በምትኩ ቡናና ሙዝ በመትከል ለአካባቢው አርሶ አደሮች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በመስራቱ የሱን አርዓያነት እየተከተሉ የሚገኙ 15 አርሶ አድሮችን ማፍራት መቻሉን አቶ ካሚል ተናግሯል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *