የከተሞች ጽዳትና ውበት በመጠበቅ ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አስታወቀ።

“ጽዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምራት ውድማ በመድረኩ ላይ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ “ጽዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል ያስጀመሩት ሀገራዊ ንቅናቄ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

በሀገሪቱ የከተማ መስፋፋት ተከትሎ በከተማ የሚኖር የህዝብ ቁጥር በየጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት በከተማ ላይ የሚመነጨው ቆሻሻ እየጨመረ መምጣቱን ኃላፊው ተናግረዋል።

በመሆኑም ይህንን ማስተዳደር የሚችል የአሰራር ስርዓትና አቅም በመፍጠር የከተሞች ጽዳትና ውበት በመጠበቅ ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ስራ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ በንቅናቄ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባ አቶ ታምራት ውድማ አሳስበዋል።

የከተማ ጽዳትና ውበት ለመጠበቅ የአረንጓዴ መሰረተ ልማቶች ማሟላት እንደሚገባ የገለጹት አቶ ታምራት ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ከከተማው ነዋሪዎች፣ ከባለሀብቶች፣ ከግልና ከመንግስት ድርጀቶች፣ ከእምነት ተቋማትና ከእድሮች ጋር በቅንጅት ሊሰራ ይገባል።

በዚህ የንቅናቄ ስራ በከተሞች የተፈጠሩ አደረጃጀቶች ሚናቸውን አጉልተው ሊያሳዩ በሚያስችል መልኩ ሊፈጸም እንደሚገባ አቶ ታምራት አስገንዝበዋል።

በጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የማስፈፀም አቅም ግንባታና መሰረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ክንፈ ሀብቴ በበኩላቸው በከተማ የሚመነጭ ቆሻሻ በአግባቡ ካልተያዘ ለጤና መታወክ መንስኤና የቱሪዝም እድገት መቀነስ ምክንያት በመሆኑ የከተማ ኢኮኖሚ እንዲቀንስ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

ቆሻሻን መልሶ የመጠቀም ባህላችን አነስተኛ ነው እንጂ 80 ከመቶ የሚሆነውን መልሶ በመጠቀም ሀብት ማፍራት እንደሚቻል በጥናት መረጋገጡን አቶ ክንፈ ጠቁመዋል።

በከተማ የሚመነጨው ቆሻሻ በወንዝ ዳር፣ በአረንጓዴ ልማትና በመንገድ ዳር መጣል በሰፊው እንደሚስተዋል የገለጹት አቶ ክንፈ ይህንን ችግር ሊቀርፍ የሚችል ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ በንቅናቄው በትኩረት መሰራት ይኖርበታል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የገጠር የጉራጌ ማህበረሰብ የሚኖርባቸው አካባቢዎች ጽዱና ውብ በሆኑበት ልክ ከተሞችም ጽዱና ውብ የማድረግ ስራ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በዞኑ የተጀመረውን የንቅናቄ ስራ እስከ ግንቦት 28/2016 ዓመተ ምህረት በሁሉም ከተሞች እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ ተቀምጧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *