ግንቦት 23/2016 ዓ.ም
የአገና ከተማ እድገት ይበልጥ ለማሳደግ ስትራቴጂክ ፕላኑን ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።

የአገና ከተማ አስተዳደር የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን ረቂቅ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በአገና ከተማ ውይይት ተደርጓል።

የአገና ከተማ በ2013 ዓ.ም ወደ ፈርጅ 3 ደረጃ የገባች ሲሆን በከተማዋ እድገት ላይ ከፍተኛ የሆነ መሻሻሎች መኖራቸው ይነገራል።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አባይነህ አየለ እንደተናገሩት ከተማዋ ፈርጅ 3 ከመግባትዋ በፊት ትጠቀመው የነበረው መሰረታዊ ፕላን ወደ እስትራቴጂክ ፕላን እንድትሸጋገር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በልዩ ትኩረት ተሰርቷል።

ጥናቱ ሲጠና የአገና ከተማ በሁሉም አቅጣጫ በእኩል እንድትለማ ታሳቢ እንደተደረገ የገለጹት አቶ አባይነህ ከዚህ በፊት በከተማው ያልነበሩ ፕሮጀክቶች በቀጣይ በዚህ እስትራቴጂክ ፕላን እንዲኖሩ ተደርጓል ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም በዛሬው እለት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት በሚሻሻሉና በሚጨመሩ ጉዳዮች ላይ በመግባባት የከተማው እድገት እንዲሻሻል ታሳቢ ያደረገ ውይይት መሆኑን አቶ አባይነህ ተናግሯል።

በዛሬው እለትም በርካታ ምክረ ሀሳቦች ከህብረተሰቡ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን ሀሳቦቹ በጥናቱ በማካተት ማስተር ፕላኑ እርክክብ ተደርጎ በአፋጣኝ ወደ ትግግበራ እንደሚገባ ጠቁመው የከተማዋ እድገት ይበልጥ ለማሳደግ ስትራቴጂክ ፕላኑን ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አስታውቀዋል ።

የጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምራት ውድማ ለአንድ ከተማ እድገት ቁልፉ ተግባር በፕላን እንዲመራ ማድረግ ነው። የአገና ከተማም ይህንን ታሳቢ ያደረ ፕላን የተሰራ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ከተደረገ በተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚቻልበት ነው።

ማስተር ፕላኑ ሲጠና ከተማው በሚመጥን መልኩ መሆኑና ትኩረት የሚሹ የኢንድስትሪ ዞን፣የወጣቶች መዝናኛ ማእከላት፣የአረንጓዴ ስፍራዎች እንዲሁም ሌሎች በከተሞች እስታንዳርድ መሰረት መካተት ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች ተካተውበታል ነው ያሉት።

በከተማው የዘላቂ መንገዶች እንዲኖሩ እንዲሁም ቀደምት አባቶች ጠብቀው ያስቆዩልን ጀፎረ በከተሞችም ጥራታቸው ተጠብቀው በማስቆየት መምሪያውም ለዚህ ተግባር ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

ፕላን ሲሰራ ገንዘብ፣ጉልበትና ጊዜ የሚፈጅ ፦ተግባራዊ ሲደረግ ደግሞ በርካታ ጉዳዮች የሚነካካ በመሆኑ ህብረተሰቡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ለፕላኑ አተገባበር የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል።

የአገና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀብቴ ዘርጋ ከተማዋ ድሮ ከ2 ቤቶች ተነስታ፣ በ2013 ዓ.ም ከተማ አስተዳደርነት አግኝታ በርካታ የመሰረተ ልማት እንቅስቃሴ እየተከናወነባት ትገኛለች።

ይሁን እንጂ እስካሁን በስትራቴጂክ ፕላን አለመመራቷ ለአስተዳደርነት አመቺ ሳይሆን የቆየ ሲሆን አሁን የተዘጋጀው ማስተር ፕላን በውስጡ የተካተቱ ተግባራቶች እንደየ ሁኔታቸው በጊዜ ሂደት የሚከናወኑ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።

አገና አድጋ ለቀጣይ ትውልድ ምቹ ከተማ ለማስረከብ ከአሁንኑ በፕላንና በህግ አግባብ መመራት አለባት ያሉት አቶ ሀብቴ ፕላንና ህግን ሳይጣስ የማህበረሰባችን ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ከተማው እናለማለን ነው ያሉት።

የጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ሸሚማ ለሻድ በበኩላቸው ይህ እስትራቴጂክ ፕላን ለ10 አመት የሚቆይ ሲሆን የዛሬ 10 አመት አገና ከተማን በልማት ተቀይራ የምትታይ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በከተሞች ህግ ማቀፍ ተመርተው ህገ ወጥነትን ለማስቀረት፣ውብና ማራኪ ከተሞች እንዲፈጠሩ፣በየ ጊዜው እድገታቸው እንዲጨምርና ለኑሮ አመቺ ለማድረግ በማስተር ፕላን መመራት አለባቸው ያሉት ወ/ሮ ሸሚማ መምሪያውም በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ አካላት እንደተናገሩት ከተማው በየጊዜው በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲፈቱ የቆየ ሲሆን ከዚህ በፊትም በስትራቴጂክ ፕላኑ ብትመራ የበለጠ መልማት ትችል እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህ ስትራቴጂክ ፕላን የቀረቡ ጉዳዮች አብዛኞቹ ትክክል መሆናቸውና በቀጣይ ተጨማሪ የሚሆኑ ተግባራት በማካተት ለፕላኑ ትግበራ የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።

በውይይቱ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣የሀይማኖት አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣የንግዱ ማህበረሰብ፣አካል ጉዳተኞች፣የከተማው ነዋሪዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *