የህብረት ስራ ማህበራት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የበለጠ መደገፍ እና ማብቃት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።


የህብረት ስራ ማህበራት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የበለጠ መደገፍ እና ማብቃት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

የጉራጌ ዞን ህብረት ስራ ልማት ጽ/ቤት የህብረት ስራ ማህበራት የሪፎርምና የንቅናቄ መድረክ የህብረት ስራ ማህበራት ለሁለንተናዊ ብልጽግና በሚል መሪ ቃል በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በዚህ ወቅት እንዳሉት የዞናችን ማህበረሰብ በህብረት ሰርቶ ለትልቅ ደረጃ መድረስ የሚችል ህዝብ ቢሆንም በህብረት ስራ ማህበራቶቻችን ግን በቂ ውጤት ማምጣት አለመቻላቸው አንስተዋል።

ይህንን ለማካካስ በቀጣይ የህብረት ስራ ማህበራት ያሉበት ቁመና በመገምገም፣ኦዲት በማድረግ፣ሀብታቸው እንዳይባክን የይዞታ ማረጋገጫ በመስጠት፣አባላት በማፍራት እና ሌሎችም አስፈላጊውን ትኩረት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል።

የዞኑ የህብረት ስራ ማህበራት ወደ ቁመናቸው ተመልሰው ለህብረተሰቡ በቂ ጥቅምና አገልገሎት መስጠት እንዳለባቸውና ግልጸኝነትን በማስፈን ህብረተሰቡ በእነሱ ላይ እምነት እንዲኖረው መስራት ይገባል ብለዋል።

አቶ ላጫ አክለውም የህብረት ስራ ማህበራት የህብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የበለጠ መደገፍ እና ማብቃት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው የህብረት ስራ ማህበራቶቻችን የህብረተሰቡ ችግር በተጨባጭ የሚቀይሩና በሀገር አቀፍም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት አለበት።

በዞናችን በአጭር ጊዜ፤በትንሽ ገንዘብ ተነስተው ዛሬ ትልቅ ደረጃ የደረሱ ማህበራት እንዳሉ የተናገሩት አቶ አበራ መሰል አይነት ማህበራት በማፍራት ዞናችን የሚመጥኑ ስራዎች መስራት ይገባል ሲሉ ተናግሯል።

ለአብነትም ከዚህ በፊት ብዙ ቅሬታዎች የነበሩበት አድማስ ዩኒየን አሁን ችግሮችን ለማረም እያደረገ ያለው ጥረት እና አግኖት ዩኒየን ደግሞ የጀመራቸው ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ አማን ረሺድ የጉራጌ ማህበረሰብ በህብረት ሰርቶ በህብረት የመለወጥ ተምሳሌነቱን አስጠብቆ ማስቀጠል አለበት ብለዋል።

ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ ለዘርፉ ውጤታማነት አመራሩ በትኩረት እንዲደግፍ የተናገሩ ዳይሬክተሩ ህብረት ስራ ማህበራት ያላቸው ሀብት በመለየት ወቅቱንና አካባቢያቸው የሚመጠን ስራ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ህብረት ስራ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት ወምባርጋ የህብረት ስራ ማህበራት ለአርሶ አደሩ አስፈላጊውን ግብአትና ብድር በአካባቢው በማቅረብ በዘርፉ ምርታመነትን እንዲያድግ ማድረጋቸው ገልጸዋል።

ዘርፉ የዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር፣የህብረተሰቡ የቁጠባ ባህል የበለጠ እንዲዳብር የሚያደርግ አምራቹ ላመረተው ምርት ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እና ለሸማቹ ማህበረሰብ አስፈላጊ የሆኑ የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ሚናቸው እየተወጡ እንደሆነ አቶ ምህረት አብራርተዋል።

በቀጣይ የአባላት ተጠቃሚነትን ያረጋገጡ ህብረት ሥራ ማህበራትን እውን ለማድረግ፣በአደረጃጀት፣ በአመራር፣ በአሰራር፣ በአገልግሎት አሰጣጥ የነበሩ ችግሮች በሪፎርሙ ንቅናቄ እንዲፈቱ በማድረግ ማህበራት ተወዳዳሪ የሆኑ፣ የገበያ ድርሻቸው ያደገ፣ የፋይናነስ አቅም እንዲኖራቸው በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በውይይቱ የተሳተፊ አካላት እንዳሉት ህብረት ስራ ማህበራት ለህብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግለት ከፍተኛ በመሆኑ በቂ በጀት በመመደብ፣የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ስለጠና በመስጠት፣ብቁ የሰው ሀይል በመመደብ ዘርፉ መደገፍና ማብቃት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በዞኑ አብዛኛው ህብረት ስራ ማህበራት በትንሽ ገንዘብ ተነስተው ዛሬ ግን ትልቅ ሀብት ያመጡ ቢሆንም መድረስ ያለባቸው ቦታ የአለመድረሳቸው ምክንያት ትኩረት አለመስጠትና ችግራቸው መፍታት ስላልተቻለ መሆኑ አንስተዋል።

ህብረት ስራ ማህበራት ካፒታላቸው የበለጠ ለማሳደግ ዩኒየኖች ጋር ትስስር መፍጠር እና የህብረተሰቡ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የድርሻቸው እንዲወጡ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *