ጉልባማ ከግሊመር ኦፍ ሆፕ ከተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በ2023 የተሰሩ የልማት ስራዎች ርክክብና በ2024 በመከናወን ላይ የሚገኙ ተግባራት ያሉበት ደረጃ ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በመስክ ምልከታ ወቅት እንደገለጹት የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ከግሊመር ኦፍ ሆፕ ጋር በመተባበር በትምህርት፣ በግብርና በጤናና በማህበር የተደራጁ ሴቶች ብድር በማመቻቸት ገቢ የሚያስገኙ ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ በማስቻል የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት የሚደነቁ ናቸው፡፡

ጉልባማ የጀመራቸው የትምህርት ቤት፣ የጤና ኬላዎችና የሌሎችም ፕሮጀክቶች ግንባታ በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት እንዲውሉ እያደረገ ያለበት መንገድ በጣም አስተማሪ በመሆኑ በምርጥ ተሞክሮነት ተወስዶ በዞኑ በሁሉም አካባቢ ሊሰፋ እንደሚገባ ምክትል አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡

ለአርሶ አደሮች ብድር በማመቻቸት በሚያገኙት ገቢ ኑሮዋቸውን ሊያሻሽሉ የሚያስችሉ የዶሮና የበግ እርባታዎች፣ንብ ማነብ እንዲሁም የተሻሻሉ የድንች ዝርያዎች በመትከል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች በመሆናቸው በቀጣይ ይህንን በማስፋት የዞኑ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ በትኩረት እንደሚሰሩ አቶ አበራ አብራርተዋል፡፡

የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቅባቱ ተሰማ በበኩላቸው ጉልባማ ከአባላቱ መዋጮ እና ከረጂ ድርጅቶች ከሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ህብረተሰቡ በማስተባበር በርካታ የልማት ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ግሊመር ኦፍ ሆፕ የተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅ ከጉልባማ ጋር በመተባበር ከባለፉት 3 ዓመታት ጀምሮ በምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ እና በጉራጌ ዞን በጉመር ወረዳ ከአምና ጀምሮ የህብረተሰቡ ችግር የሚፈቱ የልማት ስራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ከባለፈው አመት ጀምሮ በጉመር ወረዳ በ11 ቀበሌዎች 157 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚደረግባቸው የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች በውሃ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በኑሮ ማሻሻል፣ በግብርናና በሌሎችም የህብረተሰቡ ችግር በመቅረፍ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተቀሜታ ያላቸው ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

እነዚህም በ10 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች መማሪያ ዘመናዊ ህንጻዎች ከነ መጸዳጃ ቤቶች፣ 3 ጥልቅ የጉድጓድ ውሃ፣ 3 ትራንስፎርመሮች በግዢ ሂደት ላይ የሚገኙ እንዲሁም 50 ሚሊዮን ብር ለአርሶ አደሩ ብድር በማመቻቸት ሰርተው ብድሩን በመክፈል ኑሮዋቸውን እንዲያሻሽሉ እየተደረገ ያለው ጥረት በተጨባጭ የአርሶ አደሩ ሕይወት እንደሚቀይር አቶ ቅባቱ አስገንዝበዋል፡፡

በቀጣይ የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ሪፎርም የማድረግ ስራ ሲጠናቀቅ ተጨማሪ አባላት በማፍራት ፣ ባለሀብቱንና መላው የጉራጌ ህዝብ በማስተባበር የራሱ ገቢ በማሳደግ የብሄረሰቡ ባህልና ቋንቋ በማሳደግና የህብረተሰቡ መሰረታዊ ችግሮች የሚቀርፉ የልማት ስራዎች በመስራት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በመስክ ምልከታ ወቅት አግኝተን ያነጋገርናቸው አንዳንድ የልማቱ ተጠቃሚዎች በሰጡት አስተያየት ጉልባማ ከግሊመር ኦፍ ሆፕ ጋር በመተባበር ባመቻቸላቸው የብድር አገልግሎት ተጠቅመው ደሮና በግ በማርባት፣ ንብ በማነብ፣ በጋሮ አትክልትና የተሻሻለ የድንች ዝርያ በመትከል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አክለውም ልጆቻቸው በጥሩ ትምህርት ቤት እንዲማሩ፣ ሴት ተማሪዎች የንጽና መጠበቂያ ቁሳቁስ መመቻቸቱ እንዲሁም ሴት ተማሪዎች በኢንቫሮመታል ክበብ ተደራጅው በት/ቤት ግቢ ገቢ የሚያስገኙ የጓሮ አትክልትና ቅመማቅመም በመትከል ተጠቃሚ በመሆናቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ከግሊመር ኦፍ ሆፕ ጋር በመተባበር የተጠናቀቁ እና በሂደት ላይ የሚገኙ የልማት ስራዎች የመስክ ምልከታ ትናንት እንዲሁም ዛሬ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ወይይት ተካሂዶ የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ርክክብ በመፈጸም እና የቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *