ባለፉት ስድስት ወራት ከህብረተሰብ ተሳትፎ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ ለመንገድ ልማት ማዋል መቻሉን የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

መምሪያው የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት በወልቂጤ ከተማ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ከድር በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት ባለፉት ስድስት ወራት ህብረተሰቡ በማሳተፍ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብስብ በርካታ የመንገድ ልማት ስራዎችን በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

የጉራጌ ብሄር የመንገድ ልማት ለኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ቀድሞ በመረዳት በርካታ የመንገድና የድልድይ ግንባታ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየ ቢሆንም በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት በከፍተኛ አመራር ተደግፎ ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎት በፍትሃዊነታ በማቅረብ ህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴው በነጻነት እያከናወነ ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰሩ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ሙራድ በዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራር በመቅረፍ የአገልግሎት አሰጣጡን የማዘመን ስራ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ የትራንስፖርት ዘርፍና ምክትል የመምሪያ ኃላፊ አቶ ግሩም ወልደሰንበት የአፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት የትራንስፖርት ስምሪት ስርዓቱን በማዘን ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ፍትሃዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በዚህም በወልቂጤ መናኸሪያ የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ህብረተሰቡ ከታሪፍ በላይ ለትራንስፖርት እንዳይከፍል ማድረግ መቻሉን ያብራሩት አቶ ግሩም በቀጣይ የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት በዞኑ በሁሉም አካባቢ እንዲሰፋ በማድረግ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በዞኑ ዋና ከተማ በሆነው በወልቂጤ መናኸሪያ የተጀመረው የኢ-ቲኬቲንግ የአገልግሎት አሰጣጥ ህብረተሰቡ ከታረፍ በላይ ለትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይከፍል የሚረዳና ጥሩ ተሞክሮ በመሆኑ በሁሉም አካባቢ እንዲሰፋ የማድረግ ስራ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል፡፡

አክለውም በዞኑ ህረተሰብ ተሳትፎ በርካታ የመንግድ ልማት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይ ይህንኑ አጠናክሮ በማስቀጠል መንገዶቹ ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በኃላፊነት ተንከባክቦ የመጠበቅ ተግባር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ተናግረዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *