በዞኑ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት የተጎዱ ወገኖች ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ተገለጸ።


በጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አደጋና ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት በዞኑ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ድጋፎች ሲደረጉ ቆይቷል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በድጋፉ ወቅት ተገኝተው እንዳሉት በዞኑ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የሚፈጠሩ አደጋዎች ተከትሎ መምሪያው በተለያየ መልኩ ለማህበረሰቡ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ማህበረሰቡ ችግሩ ከተፈጠረ በኃላ በኢኮኖሚና በስነልቦና እንዳይጎዱ ማህበረሰቡ የመረዳዳት እሴቱን በመጠቀም ድጋፍና እገዛ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው መምሪያውና የዞኑ አስተዳደር ከቀይ መስቀል ጋር በመነጋገር ከዚህ በፊት ድጋፎች መደረጉንና በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በዛሬው እለትም ቤት የተቀጠለባቸውና በአንዳንድ ሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የሚሆን ከክልሉ ጋር በመናበብ የበቆሎና የአልሚ ምግብ ድጋፍ መደረጉንም ያነሱት አቶ አበራ አልሚ ምግቡ ወልቂጤ አካባቢ ላሉ ወገኖች ሲሆን ለወረዳዎች ደሞ እንደ የችግራቸው መጠን የበቆሎ ድጋፍ ተደርጓል ነው ያሉት።

ወቅቱ በጋና ነፋሻማ ከመሆኑ አንጻር ማህበረሰቡ ችግሮች እንዳይከሰቱ በየአካባቢው የግንዛቤ ስራ ላይ ሁሉም በትኩረት መስራት ይገባል ያሉት አቶ አበራ በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖች ሁሉም አቅሙ በሚፈቅደው ልክ እንዲያግዝና እንዲረዳዳም አሳስበዋል።

በጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አደጋና ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጊዜወርቅ አለሙ በበኩላቸው ጽህፈት ቤቱ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያት አደጋዎች እንዳይፈጠሩ የመከታተል፣ የመደገፍና ከሚመለከታቸው አካላት በጋራ በመሆን የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ግንዛቤ የመስጠት ስራ ይሰራል።

ጽ/ቤቱ በተፈጥሮ አደጋ ችግሮች በሚፈጠሩ ወቅት ከወረዳና ከቀበሌ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት በጋራ በመሆን ችግሩ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት የመከታተልና የመቆጣጠር ስራ በጋራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በዛሬው እለት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እና የፌደራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት በጋራ በመሆን ያገኛቸውን መረጃዎችን መነሻ በማድረግ በዞኑ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያት ችግር ለደረሰባቸው ወገኖች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ የበቆሎ እና ለህጻናትና ለአጥቢ እናቶች የምግብ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

ማህበረሰቡ ችግር ለደረሰባቸው ወገኖች በተለያየ መልኩ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው ማህብረሰቡ የመደጋገፍና የመተሳሰብ ባህሉን በይበልጥ በመጠቀም መተጋገዝና መደጋገፍ ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።

ድጋፉ በዞኑ ለሁሉም ወረዳዎችና ለወልቂጤ ከተማ የተደረገ ሲሆን ይህም በተለያዩ ችግሮች ለተጎዱ ለ2 ሺህ 950 ተጠቃሚዎች 424 ነጥብ 5 ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች መደረጉንም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የእሳት አደጋ እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበው ጽህፈት ቤቱም ችግሩን ለመቀነስ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ከሌሎች ጋር በመቀናጀት በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልና የፌደራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በጋራ በመሆን ለጉራጌ ዞን ለሚገኙ ተጎጂ የማህበረሰብ ክፍሎች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *