ስፖርቱን በመጠቀም የዞኑ ማህበረሰብ እሴትና ማንነትን አጉልቶ ለማውጣትና በአትሌቲክሱ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማምጣት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።


የዘቢደር አትሌቲክስ ክለብ አትሌቶች የሽኝትና የጉብኝት ፕሮግራም በዛሬው እለት በአረቅጥ ከተማ ተካሂዷል።

የዘቢደር አትሌቲክስ ክለብ በ2004 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎችን እያሳየ የመጣ ክለብ ነው።ክለቡ በአሁን ሰአትም በአረቅጥ ከተማ የሚገኝ ሲሆን ከ30 በላይ ወንድና ሴት አትሌቶች በማቀፍ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በሽኝት ፕሮግራሙ ተገኝተው እንዳሉት የጉራጌ ማህበረሰብ በንግዱ ዘርፍ የበለጠ ይታወቅ እንጂ በስፖርቱ ዘርፍም ትጉ ማህበረሰብ እንደሆነ በአለም አቀፍና በሀገር አቀፍ የሚሳተፉ የዞኑ ተወላጅ አትሌቶች አንዱ ማሳያ ናቸው።

በቀጣይ ስፖርቱን በመጠቀም የዞኑ ማህበረሰብ እሴትና ማንነትን አጉልቶ ለማውጣትና በአትሌቲክሱ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የዞኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደረግ አቶ ላጫ አስታውቀዋል።

የዞኑ ማህበረሰብ ለስፖርቱ ያለው ጥሩ አመለካከት፣የአየር ሁኔታው ምቹነት እና ዘርፋን የሚደግፉ ተቋማት እንደምቹ አጋጣሚ መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ስፖርት በዞኑ የበለጠ እንዲስፋፋና በሀገር ደረጃ እንዲተዋወቅ የኬሮድ ሩጫ ሳይቆራረጥ እንደሚካሄድ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አወል ጅሟቶ እንዳሉት አትሌቶች የእረፍት ጊዜያቸው በአግባቡ በመጠቀም የስፖርት ብቃታቸው የበለጠ ለማሳደግ መስራት እንዳለባቸው መክረዋል።

ክለቡ በየ ጊዜው መሻሻሎችን እያሳየ ሲሆን በ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባዘጋጀው በ3 ዋና ዋና ውድድሮች ላይ መሳተፉ ገልጸው ለአብነትም 40ኛው የጃን ሜዳ ሀገር አቋራጭ ውድድር ከ38 ክለቦች 11ኛ በመሆንና ጥሩ ሰአት ማስመዝገብ መቻሉ ገልጸዋል።

ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመሆን ትጥቅና ጫማ፣ፍራሾች፣ቁም ሳጥኖች ፣ምንጣፍ፣ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ብርድልብስና ሌሎችም ድጋፍ መደረጉ ተናግረው ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ምክትልና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አደም ሽኩር የበጀት እጥረት፣በቂ ሜዳና ትራክ ፣ሙሉ የማሰልጠኛ ቁሳቁስ አለመኖራቸው ፣የሴቶች ተሳትፎ ማነስ፣የተሽከርካሪ እጥረት የበለጠ ውጤት እንዳይመጣ ተግዳሮት ሆነዋል ብለዋል።

እያጋጠሙ የነበሩ ችግሮችን ከሚለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመፍታት በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ ዞኑን የሚያስጠሩ አትሌቶች ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራ አቶ አደም ገልጸዋል።

የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳት ዶክተር ፋሪስ ደሊል እንደተናገሩት ሀገራችን ሀያል ሀገር መሆንዋን የምታስመሰክርበት አንዱ የአትሌቲክስ ስፖርት በመሆኑ ዞናችንም በዘርፉ የበለጠ እንድትተዋወቅ ዩኒቨርስቲው የበኩሉን እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።

የኬሮድ ስፖርት ማህበር ፕሬዝዳን አትሌት ተሰማ አብሽሮ በዚህ ወቅት እንዳሉት ከዞኑ በወጡ አትሌቶች ሀገራችን የአለም ኦሎምፒክ ሻምፒዮና መሆን የቻለች ሲሆን አትሌቶቹም የነዚህ አትሌቶች አራያ ተከትለው መስራት እንደሚጠበቅባቸው መክረው በቀጣይ በዞኑ በሚደረገው የኬሮድ እሩጫ ላይ እንዲሳተፉ አሳስበዋል።

ዞኑ በስፖርት ልማት ዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ አሁን ያሉበት ግሎባል አትሌቲክስ የስፖርት ክለብ በአረቅጥ ከተማ የራሱ ካምፕ እንዲከፍት ጥናት ተደርጎ የተፈቀደ ሲሆን ቶሎ ወደ ስራ እንዲገባ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀል።

አትሌት አብረሀም ደምስና አትሌት ሰላም አበበ በጋራ በሰጡት ሀሳብ በየ ጊዜው ለክለቡ በሚደረጉ ድጋፎችና መሰል አይነት ክትትሎች በአትሌቲክሱ ዘርፍ ውጤት እያመጡ እንደሆነ አመላክተው በቀጣይ ደግሞ ሜዳና ትራክ በማመቻቸት፣ሙሉ የስፖርት ቁሳቁስ በማሟላት፣የሴቶች ተሳትፎ በማሳደግና ለክለቡ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች እንዲማላላቸው ጠይቀዋል።

በእለቱም ለክለቡ ድጋፍ ላደረጉ ተቋማትና ጥሩ ውጤት ላስመዘገቡ አትሌቶች የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *