በጉራጌ ዞን የተጀመረው ጤፍን በክላስተር የማልማት ስራው አበረታች በመሆኑ በቀጣይም ለሌሎች አካባቢ አርሶ አደሮች ማስፋት እንደሚያስፈልግ የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በዞኑ በክላስተር እየለሙ ያሉ የግብርና ስራዎች ምርትና ምርታማነት የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነትን እያሳደጉ እንደሆነ የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገልጿል።

በኩታ ገጠም የለማ የጤፍ ማሳ በጉራጌ ዞን በቸሃ ወረዳ የተለያዩ የክልል፣የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ባለሙያዎች እና የወረዳው አርሶ አደሮች በተገኙበት የመስክ ጉብኝት ዛሬ ተካሂዷል ።

በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የደቡብ ክልል የግብርናና ገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንዳሉት በአንድ አካባቢ የሚታዩ ምርጥ ተሞክሮዎችን ወደ ሌላ ቦታ ወስዶ የማስፋት ስራ ከተሰራ ፣የግብርና ስራው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በግብአት ከተደገፈ ሀገራችን የምግብ ዋስትና የምናረጋግጥበት ወቅት አጭር እንደሚሆን ገልፀዋል።

የጉራጌ ዞን ከዚህ በፊት ከሚታወቅባቸው የእንሰትና የፍራፍሬ ምርቶች በተጨማሪ የተጀመረው ጤፍን በክላስተር የማልማት ተግባር አበረታች በመሆኑ ለቀጣይም አስፋቶ መሰራት እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።

አርሶ አደሮቹ እየገጠማቸው ያለው የዘመናዊ ማሽኖች እና የግብአት ችግሮች ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት በትኩረት የሚሰራበት ሲሆን የተወሰኑ የግብርና ማሽኖችም በቅርቡ ለቸሀ ወረዳ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

የግብርና ስራውም ለወጣቶች እና ለሴቶች የስራ እድል እየፈጠረ በመሆኑ በትኩት እንዲሰራበት አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት በየ ጊዜው የሚደረጉ የመስክ ጉብኝቶች በአንድ አካባቢ የተሰሩ ስራዎች ወደ ሌላ ቦታ ወስዶ ለመስራትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ አላማ ያላቸው ናቸው ብለዋል።

አቶ መሀመድ በሀገራችን በሰሜኑ ክፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት በግብርና ስራው ላይ ተጽእኖ እንዳይኖር ታሳቢ በማድረግ በግብርና ስራው ላይ ትኩረት ተደርጎ በመሰራቱ በግብርና ስራው አመርቂ ለውጦች ታይተዋል ብለዋል።

አክለውም አርሶ አደሩ ጊዜውና ጉልበቱ የሚቆጥቡ ዘመናዊ ተክኖሎጂዎችን ተጠቅመው እንዲያርሱ በተደረገው ጥረትም 42 ትራክተሮች በግዢ እና እስከ 256 ትራክተሮች ደግሞ በረጅም ጊዜ ክፍያ ወደ ዞኑ ገብተው እንዲያርሱ መደረጋቸው አስታውሰው በቀጣይ የከአርሶ አደሩ የሚነሱ የቴክኖሎጂና የግብአት ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል ።

የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸምሱ አማን በበኩላቸው በዞኑ በመኸር እርሻ ወቅት 142 ሺ 728 ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈኑንና ከዚህ ውስጥ 1መቶ 11ሺ 826 ሄክታር መሬት በክላስተር መልማቱን አብራርተዋል ።

በዞኑ ከ78 ፐርሰንት በላይ በክላስተር የለሙ ሲሆን ጤፍ፣ ቦለቄ ፣ስንዴ፣ገብስ እና ሌሎችም መሰረት ተደረገው የተሰሩ መሆናቸው አስገንዝበዋል።

በዞኑ ጤፍ አምራች ከሆኑ ወረዳዎች አንዱ ቸሀ ወረዳ በመሆኑ በዘንድሮው አመትም ከዚህ በፊት ያለሙ የነበሩ መሬቶችን በመለየት ጾማቸው እንዳያድሩ ተደርጓል ሲሉ ገልጸዋል።

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የደቡብ ክልል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ፈጠነ በጉራጌ ዞን 7መቶ ዲኤ ሙያተኞች በመሰረታዊ የግብርና ስራዎችን ተከታታይ ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።

ከእነዚህም የቸሀ ወረዳ አርሶአደሮች በአንድ መስኮት የግብርና ግብአት በቅርቡ እንዲያገኙ የግብርና ማእከል የተከፈተ ሲሆን በሚደረጉ የግብርና እንቅስቃሴዎች አመርቂ ለውጥ እየታየ እንደሆነም አቶ ሙሉጌታ ፈጠነ አመላክቷል ።

ወጣት አብድልሀዲ ደሊል የዱቢሳ ቀበሌ አርሶ አደር እና አንዳምላክ ንዳ የሸሬ ቀበሌ አርሶ አደር ሲሆኑ ሁለቱም በሰጡት አስተያየት በክላስተር በቆሎ፣ ጤፍ ፣ሽምብራ፣ቦለቄ እና ሌሎችም በስፋት እንደሚያመርቱም አሳውቀዋል።

በክላስተር በማልማታቸው የእርስ በእርስ እውቀታቸው በመለዋወጥ እና በጋራ እንዲሰሩ እገዛ እያደረገላቸው በመሆኑ ኑሮዋቸው ላይ ለውጥ እያመጣላቸው እንደሆነም ገልጸዋል።

በመስክ ጉብኝቱ በም/ር/መስ/ ማዕረግ የደቡብ ክልል የግብርናና ገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ፣የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ አርሽያ አህመድ፣ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል፣የጉራጌ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ክፍሌ ለማ ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች እንዱሁም አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው ።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *