በጉራጌ ዞን የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ተግባር የገቡ 335 ፕሮጀክቶች ከ4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገብ እንደቻሉ የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።

የዞኑ የኢንቨስትመንት ስትሪንግ ኮሚቴ የፕሮጀክቶቹ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል በዞኑ የእንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማበረታታት በዘርፉ የነበሩ የአሰራር ችግሮች በመቅረፍ አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለፃ የዞኑ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በፕሮጀክቶቹ አካባቢ የሚስተዋሉ የመብራት፣ የመንገድና የውሃ ችግሮች ለመፍታት ባለሀብቶችን ጨምሮ የወረዳና የዞን አስተዳዳሪዎች በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል።

በዞኑ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ከተሰጣቸው 389 ፕሮጀክቶች ውስጥ 335 ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር በመግባት 4 ቢሊዮን 817 ሚሊዮን 177 ሺህ 664 ብር ካፒታል አስመዝግበዋል ብለዋል።

ኢንቨስትመንቶቹ በሚገኙባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች ለመፍታት ለህብረተሰቡ በፕሮጀክቶች ጠቀሜታ ላይ ግንዛቤ መፍጠር ይገባል ብለዋል።

የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘነበ ደበላ በበኩላቸው የዞኑ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እያደገ የመጣ ሲሆን ለኢንቨስትመንት ከተፈቀደ 8ሺህ 109 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት 5ሺህ 545 ሄክታር መሬት ለምቷል ብለዋል።

እንደ አቶ ዘነበ ገለጻ ወደ ተግባር በገቡ ፕሮጀከቶች አማካኝነት 20 ሺህ 450 ዜጎች በቋሚነት እና በጊዜያዊነት የስራ እድል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

የቸሃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙራድ ከድር በሰጡት አስተያየት ወረዳው ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ በመሆኑ መዋዕለ ነዋያቸው የሚያፈሱ ባለሀብቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው።

አብዛኞቹ ባለሀብቶች በማኑፋክቸሪንግና በግብርና ስራ የተሰማሩ ሲሆን ፕሮጀክቶቹ የስራ እድል ከመፍጠር በተጨማሪ የስራ ግብርና የጡረታ መዋጮ ገቢ እንደሚያስገኙ አቶ ሙራድ ገልጸዋል።

በመሆኑም ፕሮጀክቶቹ የሚያቀርቧቸው የማስፋፊያ እና ከማህበረሰቡ የሚገጥማቸው አለመግባባቶች ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

አቶ መኮንን ኃይሌ የጸደይ ውኃ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ አቶ አክሊሉ አሰፋ ደግሞ የሳቲያ ሳይት ፋርም ስራ አስኪያጅ ናቸው።

እንደ ስራ አስኪያጆቹ ገለጻ ፕሮጀክቶቹ የአካባቢው ማህበረሰብ በስራ እድል ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

የስራ እድል ተጠቃሚዎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ከመሆን ባሻገር በንድፈ ሀሳብ ያገኙት እውቀት ወደ ተግባር ለመለወጥ አስችሎናል ብለዋል።

በዕለቱ የጸደይ ውሃ፣ ዋው ውሃ፣ ሳቲየሰ ሳይት ፋርም፣ ዲፕረም አክሲዮን ማህበርና ሌሎችም ፕሮጀክቶች በስትሪንግ ኮሚቴውና በሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎችና በሚመነከታቸው አካላት ተጎብኝተዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *