በበጀት አመቱ በዞኑ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ልማት ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መስራቱን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

መስከረም 07/2015 ዓ.ም

በበጀት አመቱ በዞኑ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ልማት ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መስራቱን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

ይህ የተገለጸው የጉራጌ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 8ኛ አመት 22ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ነው።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ወይዘሮ አርሺያ አህመድ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት በ2014 በጀት አመት የአስፈጻሚና የዳኝነት አካላት እቅድና ሪፖርት በሶስቱም ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴዎች አማካኝነት በመመርመር ግብረ መልስ በመስጠት አስፈላጊውን የክትትል ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን የአካልና የመስክ ምልከታ በተመረጡ ሴክተሮች እስከ ታችኛው መዋቅር በማካሄድ መምሪያዎች በመመዘን ደረጃ የመስጠት ስራ ተሰርቷልም ነው ያሉት።

በአፈጻጸም ሂደት ላይ የሚስተዋሉ ቅሬታዎችን በወቅቱ ተለይተው እንዲቀርብ በማድረግ ምላሽ እንዲያገኙ መሰራቱንም ገልጸዋል።

የዞኑ ምክርቤት የኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ ሃይል ተግባር ከሁሉም የግብረ ሃይሉ አካላት እስከ ታች በመውረድ የመንግስትና የህዝብ ሃብት ከብክነት የመከላከልና የባከነውን የማስመለስ ስራ መሰራቱንም ክብርት አርሽያ አህመድ አመላክተዋል።

የጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል የ2014 በጀት አመቱ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት በበጀት አመቱ በበልግ ወቅት በአዝርትና በስራስር ሰብሎች ከለማው 66ሺ 663 ሄክታር መሬት 9ሚሊዮን 479 ሺህ 505 ኩንታል ምርት መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።

በተመሳሳይ በመኸር እርሻ 143ሺ 203 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር በመሸፈን በዚህም 7ሚሊዮን 307 ሺህ 613 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደተቻለ በሪፖርቱ አመላክተዋል።

የዞኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሳደግ 36 የእጅ፣ 59 መለስተኛና 17 ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ግንባታ ስራ ተሰርቷል ብለዋል አቶ መሀመድ።

በመንገድ፣ በድልድይ ግንባታና ጥገና እንዲሁም የደን ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች ከህዝብ፣ ከአከባቢ ተወላጅ ባለሀብቶችና ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በጉልበት ተሳትፎ፣ በቁሳቁስ ድጋፍ መሰራቱን ገልጸው ይህም በገንዘብ ሲተመን 140 ሚሊዮን 621 ሺህ 579 ብር የሚገመት ተሳትፎ ማድረግ ተችሏልም ብለዋል።

በጀት አመቱ ከሁሉም የገቢ አርእስቶች 1ቢሊዮን 706 ሚሊዮን 515 ሺህ 543 ብር መሰብሰብ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን ከ2013/2014 በጀት አመት ጋር ሲነጻጸር የ304 ሚሊዮን 814 ሺ 527 ብር ብልጫ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

በከተማና በገጠር በስራ እድል ፈጠራ በቋሚና በጊዜያዊ 62ሺህ 764 የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ 48 ሺህ 33 የስራ እድል መፍጠር ተችሏልም ብለዋል።

አቶ መሀመድ አክለውም በትምህርት ልማት ስራ በጉራጊኛ አፍ መፍቻ ቋንቋ በ11 ወረዳዎች፣ በ22 የቅድመ 1ኛ ጣቢያዎች 1ሺ 194 ተማሪዎች የፊደል ገበታ የሙከራ ትምህርት ከመስጠት ባሻገር ለቅድመ 1ኛ ተማሪዎች የመምህሩ መማሪያና የ1ና2 የተማሪዎች መማሪያ መጽሀፍት የማስማማት ስራ መጠናቀቁንም ጠቁመዋል።

በቀቤንሲና ሊቢዲሶ ከ1እስከ 6ኛ ክፍል የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሐፍት የማዘጋጀትና የማስማማት ስራ በመስራት፣ መጽሐፍቱ በማባዛት ለትምህርት ቤቶች ማቅረብ መቻሉንም ገልጸዋል ።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ ከ7ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በአፍ መፍቻ ቋንቋ በማዘጋጀት ለማሳተም የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እየተሰሩ ይገኛልም ነው ያሉት።

በጤናው ዘርፍ የእናቶች ሞት ከመቀነስ አንጻር የቅድመ ወሊድ ክትትል አገልግሎት ለ49 ሺ 413 እናቶች አገልግሎት መስጠት መቻሉን ገልጸው ለ50 ሺ71 እናቶች በጤና ተቋም የወሊድ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓልም ብለዋል።

በበጀት አመቱ በዞኑ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ልማት ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን መስራቱን አቶ መሀመድ ገልጸዋል።

ጉባኤው በነገው እለትም በተያዙ አጀንዳዎች ይመክራል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *