ገቢን የመሰብሰብ አቅም በማሳደግና የዞኑ ውስን ሀብት ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ በመጠቀም የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳዳር አስታወቀ።

መስከረም 06/2015
ገቢን የመሰብሰብ አቅም በማሳደግና የዞኑ ውስን ሀብት ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ በመጠቀም የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳዳር አስታወቀ።
የጉራጌ ዞን ፕላን ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ የ2015 በጀት አመት የሀብት ማከፋፈያ ቀመር አሰራርና የ2015 በጀት አመት የገቢ እቅድ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በወልቂጤ ከተማ ውይይት አካሂዷል ።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በመድረኩ ተገኝተው እንደገለጹት ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ከማሳደግ ጎን ለጎን መንግስት የሚመድበው ውስን ሀብት ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ በመጠቀም የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ መሀመድ ገለጻ በ2015 የተመደበው የዞኑ ውስን ሀብት በፍትሀዊነት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ከዚህም ጎን ለጎን የህብረተሰቡን አቅም በመጠቀም በልማትና በመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ የሚኖረው ተሳትፎ ለማጠናከር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የጉራጌ ዞን ፕላንና ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ከበደ ሀይሌ በበኩላቸው የሀብት ማከፋፈያ ቀመሩ የተሰራው የፌደሬሽን ምክር ቤት የቀመር መስሪያ መነሻ በማድረግ መሰራቱን ገልጸው ይህም ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ለሁሉም አከባቢ ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
መረጃዎችን ከማጥራትና ተአማኒነቱ ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ገልጸው መረጃዎችን በዴቭኢንፎ የማደራጀትና በጂአይኤስ የመረጃ ሶፍትዌር ለመስራት ጥረት የደርግ እንደነበር ጠቁመዋል።
ካለፉት አራት አመታት ጀምሮ ዞኑ ከደቡብ ክልል የሚያገኘው ድርሻ እየቀነሰ በመምጣቱ መረጃን ለማጥራት ሲሰራ እንደነበር የገለፁት አቶ ከበደ እየቀነሰ የመጣው የዞኑ ድርሻ ለማስተካከል የመረጃ አያያዝ ስርአት ማሻሻል ይገባል። ለዚህም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የመረጃ አያያዝ ጥራት ማሻሻል በዜጎች መካከል ፍትሃዊ የሆነ የበጀት ክፍፍል እንዲኖር ያደርጋልም ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ረሻድ በበኩላቸው ዞኑ የሚያመነጨውን ኢኮኖሚያዊ ገቢ አማጦ ለመሰብሰ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።
በ2015 በጀት አመት 2ቢሊዮን 3 መቶ ሚሊዮን 60 ሺ ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸው ይህም ከ2014 በጀት አመት እቅድ ጋር ሲነጻጸር የ29 ነጥብ 18 ከመቶ ጭማሪ መኖሩንም ገልጸዋል።
አክለውም የገቢ እቅዱ እንዲሳካ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉም ኃላፊው አሳስበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት የሀብት ክፍፍሉ ፍትሀዊና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትክክለኛና ጥራት ያለው የመረጃ አያያዝ ላይ በቀጣይ በትኩረት ሊሰራበት ይገባልም ብለዋል።
የዞኑ የገቢ አቅም በየአመቱ እያደገ መምጣቱ የሚበረታታ ቢሆንም ዞኑ የሚያመነጨውን ኢኮኖሚያዊ ሀብት አማጦ ከመሰብሰብ አንጻር ውስንነት በመኖሩን በጀት አመቱ የታቀደው እቅድ እንዲሳካ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ጠቁመዋል።
በመድረኩም የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል፣ የጉራጌ ዞን የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች፣ የዞን፣ የወረዳና ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የጽህፈት ቤቱ ባለሙያዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *