በስነ ምግባር የታነጸ ብቁና ስራ ፈጣሪ ትውልድ ለማፍራት ወላጆች የልጆቻቸው የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸዉን መከታተል እንደሚጠበቅባቸዉ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ገዙሜ አሳሰቡ።

መስከረም 03/2015

በስነ ምግባር የታነጸ ብቁና ስራ ፈጣሪ ትውልድ ለማፍራት ወላጆች የልጆቻቸው የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸዉን መከታተል እንደሚጠበቅባቸዉ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ገዙሜ አሳሰቡ።

በጉራጌ ዞን የ2015 የትምህርት ሳምንት መርሀግብር በቸሀ ወረዳ አዘርና ሲሰ ቀበሌ በሳህለማሪያም ንጋቱ መታሰቢያ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተካሄደ።

የ2015 ዓ .ም የትምህርት ሳምንት በዓል ያስጀመሩት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ገዙሜ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ተማሪዎች በእውቀት የበለፀጉና በስነምግባር የታነጹ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

ስርዓተ ትምህርቱ ባለፉት የትምህርት ስርዓት ላይ የነበሩ ችግሮች በመዳሰስ፣ በመገምገምና በማጥናት ተማሪዎች ለተሻለ ደረጃ ለማዘጋጀት እንደሚያስችል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።

ወላጆች የልጆቻቸውን የትምህርት ቤት ቆይታ፣ ክህሎት እና ከመምህራኖቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመከታተል ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የበኩላቸው ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ተማሪዎች የነገይቱን ሀገር ተረካቢ በመሆናቸው ጊዜያቸው በአግባቡ በመጠቀም ብቁ፣ ተወዳዳሪ እና ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በበኩላቸው በስራ ላይ የዋለው አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት የሚጠይቀው የሰው ሀብት ለማፍራት የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ሲሆን ተማሪዎች ብቁ ስራ ፈጣሪና በስነምግባር ታንጸው እንዲያድጉ ያስችላል ብለዋል።

የፍኖተ ካርታው ከ1 እስከ 6ኛ ክፍል በአንደኛ ደረጃ፣ ከ7ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በመለስተኛ 2ኛ ደረጃ እና ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በ2ኛ ደረጃ የሚቀጥሉ ሲሆን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ማካተቱንም ገልጸዋል።

በጥራት ላይ የተመሰረተው አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ሀገሪቱ የጀመረችው ለውጥ የሚያጠናክርና አቅም ያለው የሰው ሀይል በሁሉም መስኮች ለመፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

እንደ አቶ መሀመድ ገለፃ አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በ2014 ዓ.ም በዞኑ በተመረጡ 12 ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን በ2015 በዞኑ በሚገኙ በ628 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በዛሬው እለት በይፋ ተጀምሯል።

የቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች ለመደበኛ ትምህርት በማዘጋጀት የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በክረምት ወራት ለቅድመ 1ኛ ደረጃ ተማሪዎች 306 አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተዋል ብለዋል።

በ2015 ዓ.ም በዞኑ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ 463 ሺህ 35 ህጻናት ወደ ትምህርት ገበታ ለማስገባት ታቅዶ 277ሺህ 240 ተማሪዎች ብቻ የተመዘገቡ በመሆናቸው በቀጣይ ህፃናቱ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲቀላቀሉ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል ።

የቸሃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸዉ በወረዳው ዘመኑን የሚመጥኑ የትምህርት ተቋማት ለመገንባት የአካባቢው ማህበረሰብና ባለሀብቶች የሚያደርጉት ተሳትፎ የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው ባለሀብቶች ከተገነቡ የትምህርት ተቋማት መካከል የሳህለማሪያም ንጋቱ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠቃሽ ሲሆን ትምህርት ቤቱ በሰው ሀይልና በቁሳቁስ በማሟላት ለመማር ማስተማር ስራ ምቹና ተመራጭ መሆኑም ተናግረዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የትምህርት ተቋማት ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ በማድረግ ለትምህርት ጥራት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *