የአገና ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር የሚቀርፉ የተለያዩ ሀገር በቀል እውቀቶች በማሻሻል ለማህበረሰቡ እያሸጋገረ እንደሚገኝ ኮሌጁ አስታውቋል ።

መስከረም 01/2015

የአገና ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር የሚቀርፉ የተለያዩ ሀገር በቀል እውቀቶች በማሻሻል ለማህበረሰቡ እያሸጋገረ እንደሚገኝ ኮሌጁ አስታውቋል ።

ኮሌጁ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ብቁና ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ለመፍጠር ተግቶ እየሰራ ይገኛል።

አቶ ታደለ ጄቤሳ የኮሌጁ ምክትል አካዳሚክ ዲን ሲሆኑ ኮሌጁ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ሀገር በቀል እውቀቶች በመለየት፣ በማጥናትና በማሻሻል የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር መቅረፍ እንዲችሉ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለሀገር በቀል እውቀቶች የሚሰጣቸው ግምት አነስተኛ ቢሆንም ለማህበረሰቡ የሚሰጡት ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ጊዜ፣ ወጪና ጉልበት ሊቀንሱ በሚችሉባቸው ደረጃ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን አቶ ታደለ አስረድተዋል።

በቀርከሃ፣ በቀንድ፣ በቃጫና በሸክላ ስራ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በጥራትና በብዛት ማምረት እንዲችሉ ቴክኖሎጂዎቹ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ያሉት ምክትል አካዳሚክ ዲኑ ኮሌጁ ለእነዚህ ተግባራት ትኩረት መሰጠቱ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች የሚሰጣቸው ግምት ከፍ እንዲል ያደርገዋል ብለዋል።

እስካሁን በሰው ጉልበትና ኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰሩ የቆጮ መፋቂያ፣ የአምቾ መከትከቻና የቡላ መጭመቂያ ማሽኖች በመስራት ለማህበራት ማሸጋገር ተችሏል።

ኮሌጁ የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ አስር ቴክኖሎጂዎች የተለዩ ሲሆን በ2015 ለህብረተሰቡ ለማስተዋወቅ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የካይዘን አሰራር ስርዓት የሀብት፣ የጊዜና የጉልበት ብክነት የሚቀንስ በመሆኑ በዚህ የክረምት ወራት በአገና ጤና ጣቢያና በትምህርት ተቋማት ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በክረምት መርሀግብር 40 የ2ኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመሰረታዊ ኮምፒውተር ስልጠና የተሰጣቸው ሲሆን በ2015 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አጠናቀው የተቀመጡ ተማሪዎች በመደበኛው መርሀግብር እንዲሰለጥኑ ግንዛቤ በመፍጠር ቅስቀሳ እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል።

ኮሌጁ ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ፣ ማራኪና ተመራጭ ለማድረግ ለውበት፣ ለጥላና ለምግብነት ግልጋሎት የሚውሉ አንድ ሺህ 9 መቶ ችግኞች መትከል እንደተቻለ አቶ ታደለች አስረድተዋል።

ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር የኮሌጁ ማህበረሰብ በማስተባበር የአቅመ ደካሞችን ቤት ያስገነባ ሲሆን ወላጆቻቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ተበርክቶላቸዋል ብለዋል።

የ2015 ዓ . ም የስልጠና ዘመን ስራው ውጤታማ ለማድረግ የማሰልጠኛ ሰነዶችና ወርክ ሾፖች ማዘጋጀት፣ የአሰልጣኞች አቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠት እና ሁለተኛ ደረጃ አጠናቀው የተቀመጡ ተማሪዎች መረጃ በማጠናቀር የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ታደለ አስረድተዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *