የጊፋታ በዓልን ከወንድም የወላይታ ህዝብ ጋር ለማክበር መጋበዛችን የህዝባችን የአብሮነት እሴቶች ይበልጥ እንዲጎለብቱ ያደርጋል ሲሉ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል ገለጹ።

ጳጉሜ 04/2014
የጊፋታ በዓልን ከወንድም የወላይታ ህዝብ ጋር ለማክበር መጋበዛችን የህዝባችን የአብሮነት እሴቶች ይበልጥ እንዲጎለብቱ ያደርጋል ሲሉ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል ገለጹ።

ዋና አስተዳዳሪው በጊፋታ በዓል ላይ እንዲታደሙ ከወላይታ ዞን አስተዳደር የቀረበላቸውን ጥሪ በአክብሮት ተቀብለው በዕለቱ እንደሚገኙ አስታወቁ።

የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ ጊፋታ በዓል በወላይታ ብሔር ዘንድ አሮጌውን ዓመት በመሸኘት አዲሱን ዓመት የሚቀበሉበት የዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡

በዓሉ ከመስከረም 14 እስከ መስከረም 21 ቀን ድረስ የሚቆይ ሲሆን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ እየተሰራ ይገኛል።

የ2015 ዓ. ም የዘመን መለወጫ በዓል በልዩ ሁኔታ ለማክበር የተለያዩ እንግዶች እንዲታደሙ ጥሪ ተደርጎላቸዋል። ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች መካከል የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል ይገኙበታል።

የጉራጌና የወላይታ ዞን ህዝቦች ከአካባቢያቸው ባለፈ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ሲሆን ከሌሎች ወገኖች ጋር ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩ ታታሪና ስራ ወዳድ ወንድማማቾች ናቸው ብለዋል።

የእነዚህ ወንድማማቾች አንድነትና አብሮነት ይበልጥ እንዲጠናከር የጊፋታ በዓል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጉራጌ ዞን ተወላጆች በወላይታ ዞን የሚኖሩ ሲሆን በተመሳሳይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የወላይታ ዞን ተወላጆች በጉራጌ ዞን ይገኛሉ። እነዚህ ወገኖች ትስስራቸውን ይበልጥ እንዲጠናከር የጊፋታ ዘመን መለወጫ በዓል ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

በመሆኑም የወላይታ ዞን አስተዳደር በጊፋታ በዓል እንዲታደሙ መጋበዛቸው የወንድማማችነትና የአብሮነት እሴቶቻችን የሚያጠናክር መሆኑን አቶ መሀመድ ገልጸዋል።

በወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል የጉራጌ ዞን ህብረተሰብ አንድነት የሚያስተሳስሩ እና ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር አብሮ ለመኖር የሚያግዙ ስራዎች ለመስራት ልምድ የምንቀስምበት እና በደስታቸው የምንሳተፍበት በዓል ነው ብለዋል።

ዋና አስተዳዳሪው የወላይታ ዘመን መለወጫ የሆነው “ጊፋታ በዓል” የሠላም፣ የጤና፣ የአንድነትና በጋራ የምንበለጽግበት ዘመን እንዲሆንልን እመኛለሁ ብለዋል።

የወላይታ ዞን አስተዳደር የክብር እንግድነት ጥሪ ግብዣ ያቀረቡት የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊና የጊፋታ በዓል አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሳምነው አይዛ የወላይታና የጉራጌ ተወላጆች በስራ ወዳድነት የሚታወቁ ወንድማማቾች ናቸው።

የእነዚህ ወንድማማቾች አንድነትና ወዳጅነት ይበልጥ እንዲጠናከር ያስችላል ያሉት አቶ አሳምነው በወላይታ ዞን የሚገኙ የጉራጌ ተወላጆች የጊፋታ በዓል እንዲያከብሩ እያስተባበሩ መሆናቸው አውስተዋል።

በዞኑ ብልጽግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና ስነ ምግባር ኃላፊ ወይዘሮ መስከረም ደገፋ ጉራጌና ወላይታ ዝቅ ብለው ሰርተው ከፍ ብለው የሚታዩ ጠንካራና ስራ ወዳድ ብሄሮች ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም የእነዚህ ወንድማማቾች ጠንካራ የስራ ባህልና የአብሮነት እሴቶች እንዲጎለብት የሚያደርግ በመሆኑ በዓሉ በድምቀት ይከበራል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *