ሀገሪቱ የገጠማት የህልውና ዘመቻ በብቃት ለመመከት የበኩላቸው አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ በጉራጌ ዞን የሚገኙ የሙያ ማህበራት ገለጹ።

ጳጉሜን 4/2014 ዓ.ም

ሀገሪቱ የገጠማት የህልውና ዘመቻ በብቃት ለመመከት የበኩላቸው አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ በጉራጌ ዞን የሚገኙ የሙያ ማህበራት ገለጹ።

ይህን ያሉት ማህበራቱ ከጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው።

ሀገሪቱ ተገዳ የገባችበት ጦርነት በድል ለማጠናቀቅና ለጀግናው የሀገር መከላከያ ስራዊት ደጀን ለመሆን የበኩላቸው አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ የማህበሩ አባላት አረጋግጠዋል።

ከብልጽግና ፓርቲ አመራር ጋር የተደረገው ውይይት የአሸባሪው የህወሓት ቡድን አገር የማፍረስ ሴራ አስነዋሪና ጭካኔ የተሞላበት ተግባር እየፈጸመ ስለመሆኑ ብዙ መረጃዎች እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

ልማት፣ እድገትና ዲሞክራሲ የሚረጋገጠው ሀገር ሰላም ሲሆን ብቻ በመሆኑ ሁሉም በዘር፣ በሀይማኖት፣ በቋንቋ፣ በብሔር ሳይከፋፈል ለሀገሩ ህልውና በአንድነት መቆም ይጠበቅበታል ብለዋል።

የሙያ ማህበራት ለአባሎቻቸው በተለያዩ መንገዶች ሀገሪቱ ስላለችበት ሁኔታና ስለቀደመው ታሪኳ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እንሰራለን ብለዋል።

በጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ተቋማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሐም ጠና በበኩላቸው ህወሃት የሀገሪቱ ሰላም በማደፍረስና የለውጥ ጉዞ በማደናቀፍ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ለማሳደር ሲሰራ እንደነበር ገልጸዋል።

መንግስት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በማንኛውም ጊዜ ከህወሓት ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን የገለጹት አቶ አብረሐም ሀገሪቱ ተገዳ የገባችበት ጦርነት የሙያ ማህበራትና አባሎቻቸው ትክክለኛ መረጃ እንዲኖራቸው እየተሰራ ነው ብለዋል።

የዞኑ ማህበረሰብ የሀገሪቱ ሉዐላዊነት ለማስከበር ሁሉ አቀፍ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር የተናገሩት ኃላፊው በቀጣይም አንድነቱን በማጠናከር በሀገሪቱ የሚቃጡ ማናቸውም ጥቃቶች በብቃት ለመመከት ድጋፋቸው ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

እንደ አቶ አብረሀም ገለጻ የውይይት መድረኩ የሙያ ማህበራት አመራሮች ከዚህ ቀደም ስለሀገሪቱ ከነበራቸው መረጃ በተጨማሪ በውይይት መድረኩ ያዳበሩት መረጃ ተጠቅመው ለአባሎቻቸው ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላቸዋል።

በቀጣይም የአሸባሪ ቡድኑና ደጋፊዎች ድርጊት ከማውገዝ ባለፈ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች እና የመንግስት አቋም መረጃ እንዲኖራቸው ማህበራቱ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በመድረኩ የጉራጌ ዞን አካል ጉዳተኞ፣ የዞኑ አረጋዊያንና የዞኑ መምህራን ማህበር እንዲሁም ረጂ ድርጅቶች፣ የወጣትና ሴት አደረጃጀቶች ተሳትፈዋል ሲል የዞኑ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ዘግቧል።

እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub:- https://youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36CxQ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *