በወልቂጤ ዩንቨርስቲ ስፔሻለይዝድ ሆስፒታል ከአእምሮ ህመም ጋር ተያይዞ በአቅራቢያቸው የተሻለ የህክምና አገልግሎት በማግኘታቸው ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተገልጋዮች ገለፁ።

ጳጉሜ 04/2014 ዓ.ም

በወልቂጤ ዩንቨርስቲ ስፔሻለይዝድ ሆስፒታል ከአእምሮ ህመም ጋር ተያይዞ በአቅራቢያቸው የተሻለ የህክምና አገልግሎት በማግኘታቸው ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተገልጋዮች ገለፁ።

የአእምሮ ህሙማን ተገቢዉን የህክምና ክትትል በማግኘት አገግመው አምራች በመሆን ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን መለወጥ እንዲችሉ ሆስፒታሉ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የአእምሮ ታማሚ ሲባል በብዙ ሰዎች ዘንድ ልብሱን አውልቆ የሚሮጥ፤ በሌላው ላይ አደጋ የሚያደርስና የሚተናኮል እንዲሁም የፈጣሪ ቁጣ የደረሰበትና የማይድን ህመም ተደርጎ እንደሚታይ የስነ አእምሮ ሃኪሞች ይገልፃሉ፡፡

በወልቂጤ ዩንቨርስቲ ስፔሻለይዝድ ሆስፒታል በአእምሮ ህክምና ክፍል ሲገለገሉ ካገኘናቸው ታካሚዎች መካከል ወጣት ምንተስኖት ይማል የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ ነው።

በጓደኞቹ ግፊት እንደቀልድ የጀመረው የጫት ሱስ ቀስ በቀስ በማደጉ የሀሺሽና የሌሎችም ደባል ሱሶች ተጠቃሚ ሆኖ ቆይቷል። በዚህም ለከፍተኛ ጤና መታወክ መጋለጡን የሚናገረው ወጣት ምንተስኖት ራሱን መቆጣጠር አቅቶት አስቸጋሪ ጊዜያትን ከማሳለፉም በተጨማሪ በቅርቡ በራሱ ላይ የአካል ጉዳት አድርሷል።

አሁን ላይ በሆስፒታሉ የአእምሮ ህክምና ክፍል በተደረገለት የህክምና ክትትል ከህመሙ እያገገመ ከመሆኑም ባሻገር በሱ መታመም የመጣ አብረውት ለረጅም አመታት ሲታመሙ የቆዩትን እናቱን ለመካስ ተስፋን ሰንቋል።

ወ/ሮ ገነት ግዛቸው የወጣት ምንተስኖት ወላጅ እናት ሲሆኑ በልጃቸው የአእምሮ መታወክ ምክንያት ላለፉት 10 አመታት አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፈዋል።

ከፍተኛ ወጪ በማውጣት አዲስ አበባና ሌሎችም አካባቢዎች ለህክምና ወስደውት የነበረ ቢሆንም ሊሻለው ባለመቻሉ ተስፋ ቆርጠው መቆየታቸውን ያስታውሳሉ።

ለልጃቸው አእምሮ መታወክ መነሻ ምክንያት ሱስ መሆኑን የሚያምኑት ወ/ሮ ገነት ዛሬ ላይ የልጃቸው ጤና አየተሻሻለ በማየታቸው ደስተኛ ናቸው ።

አሁን አሁን ወጣቱ ትውልድ በከፍተኛ ሁኔታ በሱስ እየተጠቃ በመሆኑ በመከላከሉ ስራ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

ወጣት አንዳምላክ አሰፋ የአበሽጌ ወረዳ ነዋሪ ሲሆን በትምህርቱ የደረጃ ተማሪ እንደነበረና በገጠመው የአእምሮ ህመም ምክንያት የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ክፍል ትምህርቱን ለሟቋረጥ ተገዷል።

ምንም እንኳን ዛሬ ላይ ከህመሙ በማገገም በተሻለ ጤና ላይ የሚገኝ ቢሆንም በእሱ መታመም እናቱን ጨምሮ ሌሎች ቤተሰቦቹ ያሳለፉትን አስቸጋሪ ጊዜ ሲያስታወስ እንባው ይቀድመዋል።

ትላንት ከራሱና ከቤተሰቦቹ አልፎ አካባቢውንና ሀገሩን ለመለወጥ ተስፋ ሰንቆ የነበረው አንዳምላክ ዛሬ ላይ በገጠመው ህመም ምክንያት ቤተሰቦቹን በማስቸገሩ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማዋል።

ዶ/ር እሸቱ ጡሚሶ በወልቂጤ ዩንቨርስቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአእምሮ ህክምና ስፔሻላስት ሲሆኑ ከአእምሮ ጤና ጋር በተያያዘ በርካታ አሉታዊ አመለካከቶች እዚህም እዚያም ሲነገሩ እንደሚስተዋሉ ገልፀዋል።

በዚህም ታማሚዎችን በወቅቱ ወደ ህክምና ተቋም አለመውሰድና በባህላዊ ህክምና ላይ ትኩረት የማድረግ ሁኔታዎች ከመኖራቸውም ባሻገር ቤት ውስጥ ለረጅም አመታት አስሮ በማስቀመጥ በታማሚዎች ላይ ተጨማሪ የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው እንደሚስተዋል አስረድተዋል፡፡
የአእምሮ ህመም እንደማንኛውም ህመም ታክሞ መዳን እንደሚቻል የሚገልፁት ዶ/ር እሸቱ በማህበረሰቡ ዘንድ በአእምሮ ሕሙማን ላይ የሚደርሰው ማግለልና መድልዎ መቅረፍ ይገባል ብለዋል፡፡

ሱስ በራሱ የአእምሮ ሕመም ከመሆኑም ባሻገር ሌሎች የአእምሮ ህመሞችን የመቀስቀስና የማባባስ ጉልበት አለው የሚሉት ዶ/ሩ በሆስፒታሉ ለታማሚዎች ልዩ ልዩ የህክምና አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በመግስትና በህብረተሰቡ ዘንድ ለአእምሮ ህክምና እና ታማሚዎች የሚሰጠውን ትኩረት ማሳደግ እንደሚገባም በመጠቆም፡፡

በሆስፒታሉ የአእምሮ ህሙማን ተገቢዉን የህክምና ክትትል በማግኘት አገግመው አምራች በመሆን ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን መለወጥ እንዲችሉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሆስፒታሉ የጥራት ቁጥጥር ክፍል ሃላፊ ዶ/ር ፍቅረፅዮን ደገሙ ናቸው ፡፡

የአእምሮ ህክምናን ጨምሮ ሌሎችም በሆስፒታሉ የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን ጥራት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የማህበረሰቡና የመላው ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል ሲል የወልቂጤ ኤፍ ኤም ዘግቦታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *