ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ ፣ተመራጭ ለማድረግና ደረጃቸው ለማሳደግ ረጂ ድርጅቶች የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተገለጸ።

ነሐሴ 29/2014

ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ ፣ተመራጭ ለማድረግና ደረጃቸው ለማሳደግ ረጂ ድርጅቶች የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተገለጸ።

ሚዛን የሰላምና ልማት ማህበር በትምህርት ተቋማት ግንባታ ላይ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

ሚዛን የሰላምና ልማት ማህበር የዞኑ ማህበረሰብ በትምህርት፣ በጤና፣ በውሃና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ ለማድረግ የተቋቋመ አገር በቀል ማህበር ነው።

የጉራጌ ዞን አስተዳደሪ ልዩ አማካሪ አቶ ፈቱ አብዶ ማህበሩ በቀቤና ወረዳ በዘቢሞላ ቀበሌ ያስገነባዉን ትምህርት ባስመረቀበት ወቅት ተገኝተዉ እንደገለጹት ሚዛን የሰላምና ልማት ማህበር በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች እያከናወናቸው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የማስፋፊያ ግንባታ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ።

ማህበሩ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በሌሎች አካባቢዎች ማስቀጠል አለበት ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የዞኑ አስተዳደር ከማህበሩ ጋር ሆኖ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ በበኩላቸዉ የትምህርት ተቋማት ወቅቱን የሚመጥን የመማር ማስተማር አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት አለባቸው ብለዋል።

በዞኑ የሚገኙ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች በመሆናቸው የትምህርት ቤቶቹን ደረጃ ለማሻሻል ማህበረሰቡ፣ ባለሀብቶችና ረጂ ድርጅቶች የሚያደርጉት ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ሚዛን የሰላምና ልማት ማህበር በገደባኖ ጉታዘር ወለኔ፣ በቸሃ እና በቀቤና ወረዳዎች ያከናወናቸው የማስፋፊያ ግንባታዎች የትምህርት ቤቶቹን ደረጃ ከማሻሻል ባለፈ የተማሪዎች ውጤት ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል።

በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸው በእነዚህ ትምህርት ተምረው ነገ አካባቢያቸውና ሀገራቸው መጥቀም እንዲችሉ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የትምህርት ቤቶች ደረጃ ዝቅተኛ መሆን፣ የግብዓት አለመሟላት፣ የወላጅና የመምህራን ክትትል ማነስ በዞኑ በ12ኛ እና በ8ኛ ክፍሎች አገር አቀፍና ክልል አቀፍ ፈተና ዝቅተኛ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑ አስረድተዋል። ይህን ውጤት ለመቀየር ወላጆች በንቃት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የቀቤና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብደላ ጀማል ማህበሩ የትምህርት ተቋማት ለማሳደግ እያደረገ ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው ብለዋል።

በወረዳው የሚገኘው ዘቢሞላ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከደረጃ በታች የነበረ ሲሆን ማህበሩ ከገነባቸው አራት የመማሪያ ክፍሎች በተጨማሪ የወረዳው አስተዳደር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በወረዳው የሚገኙ 28 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ከደረጃ በታች በመሆናቸው በቀጣይ የትምህርት ቤቶቹን ደረጃ ለማሻሻል ማህበሩ የሚያደርገው ድጋፍ መጠናከር አለበት ብለዋል።

የማህበሩ አስተባባሪ አቶ መዚድ ናሲር እንዳሉት ማህበሩ ከተመሰረተ ሁለት አመት ቢሆንም በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ከሃያ ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ፣ የትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ ግንባታ፣ የተማሪዎች ምገባና የተለያዩ ስልጠናዎች አመቻችቷል ብለዋል።

ማህበሩ የዞኑ ማህበረሰብ በዘላቂነት ተጠቃሚ ለማድረግ ግብጥሎ እየሰራ መሆኑ የገለጹት ሰብሳቢው የማህበሩ አቅም ለማሳደግ ሁሉም የማህበሩ አባል እንዲሆን ጠይቀዋል።

የዘቢሞ ቀበሌ ነዋሪዎችና ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም የነበሩ የመማሪያ ክፍሎች የፈራረሱና ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ ባለመሆናቸው በተማሪዎች ውጤት ላይ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል።

ማህበሩ የትምህርት ቤቱ ችግር በዛላቂነት ለመቅረፍ ያደረገው ጥረት የሚበረታታ እና ለሌሎች ረጂም ድርጅቶች ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።

በእለቱም የማህበሩ አባላትና አመራሮች በወልቂጤ ማረሚያ ግቢ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አካሄደዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *