ሚዛን የሰላምና ልማት ማህበር ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በቸሀ ወረዳ ያስገነባው የወሸርቤ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ ተመረቀ።

ነሐሴ 28/2014 ዓም

ሚዛን የሰላምና ልማት ማህበር ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በቸሀ ወረዳ ያስገነባው የወሸርቤ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ ተመረቀ።

የትምህርት ቤቱ መገንባት ብቁና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለመቅረጽ እንደሚያስችል ተማሪዎች ገለጹ።

በጉራጌ ዞን ረጅም እድሜ ካስቆጠሩ ትምህርት ቤቶች አንዱ በቸሃ ወረዳ የሚገኘው የወሸርቤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠቃሽ ነው።

ትምህርት ቤቱ እረጅም እድሜ ቢያስቆጥርም ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ አለመከናወኑና ትምህርት ቤቱ በቁሳቁስ አለመሟላት ዘመኑን የሚመጥን የመማር ማስተማር አገልግሎት እንዳይሰጥ አድርጎታል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ በምረቃ ስነ-ስርዓት ወቅት እንደተናገሩት በዞኑ ከሚገኙ 628 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 113 ትምህርት ቤቶች ብቻ የሚፈለግባቸውን ደረጃ ማሟላት ችለዋል።

ሚዛን የሰላምና የልማት ማህበር የትምህርት ቤቶች ደረጃ በማሻሻል ለመማር ማስተማር ስራ ብቁ ለማድረግ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ከፍተኛ መሆኑን አቶ አስከብር ወልዴ ገልጸዋል።

ማህበሩ የጀመረው የልማት ስራ የሚበረታታ በመሆኑ በቀጣይ በሌሎች ትምህርት ቤቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመቅረፍ መስራት እንዳለበት ኃላፊው ተናግረዋል።

የቸሀ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸው ማህበሩ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባው የወሸርቤ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ የትምህርት ቤቱ የመማሪያ ክፍሎች ችግር ለመቅረፍ ያስችላሉ ብለዋል።

ማህበሩ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት አኩሪ በመሆናቸው በቀጣይ ማህበሩ የሚያከናውናቸው ማናቸውም የልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑና የወረዳው ድጋፍ ሲሻ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚደረግለት አቶ ሙራድ አረጋግጠዋል።

ዋና አስተዳዳሪው ከማህበሩ በተጨማሪ ሶስት የመማሪያ ክፍሎች በማስገንባት በትውልዱ ላይ አሻራ ላኖሩ ለአቶ ኑረዲን ነጋሽና ለሌሎች ባለሀብቶችና ረጂ ድርጅቶች ምስጋና አቅርበዋል።
የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ መዚድ ናሲር በበኩላቸዉ ማህበሩ በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ችግር ለማቃለልና የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

ለምረቃ የበቃው የወሸርቤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ ሙሉ ወጪው ሙስሊም አይድ ከተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብና ወጪ እንዲጠናቀቅ ተደርጓል ብለዋል።

ተማሪ አብዱሀፊዝ ሃያቱ እና ጀሚል መሀመድ በወሸርቤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ እና የ7ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው።

እንደተማሪዎቹ ገለጻ የትምህርት ቤቱ ግንባታ መፈራረስ ሙሉ ትኩረታቸው በትምህርት ላይ እንዳያደርጉ ማነቆ ፍጥሮባቸዉ እንደነበረም አስታዉሰዋል።

ይሁን እንጂ ሚዛን የሰላምና ልማት ማህበር ደረጃቸው የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች አስገንብቶ ማስረከቡ በቀጣይ ውጤታማና ብቁ እንድንሆን ያስችለናል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *