የጉራጊኛ ቋንቋን ከመጥፋት አደጋ ለመታደግ የትምህርት እና የሚዲያ ቋንቋ ለማድርግ የዞኑ መንግሰት የሚጠበቅበትን ተግባር እያከናወነ መሆኑን የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ መሀመድ ጀማል ገለፁ፡፡

ከተያዘው ሐምሌ ወር ጀምሮ የጉራጊኛ ቋንቋ ስርጭት አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት የወልቂጤ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

የጉራጊኛ ቋንቋ የመጥፋት አደጋ ውስጥ ካሉ ቋንቋዎች አንዱ ነው ያሉት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ መሀመድ ጀማል ለዚህ ምክንያት ደግሞ ቋንቋው የስራ የትምህርት እና የሚዲያ ቋንቋ ማድረግ ባለመቻላችን ነው ብለዋል፡፡

ስለሆነም ቋንቋን ለማልማትና ከጥፋት ለመታደግ የሚዲያና የትምህርት ቋንቋ ለማድረግ የዞኑ መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የወልቂጤ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ከተቋቋመ ከ13 አመታት በላይ ቢያስቆጥርም በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን በጉራኛ ቋንቋ የስርጭት አገልግሎት መስጠት አለመቻሉን ጠቁመው አሁን ላይ ግን በቅርቡ የስርጭት አገልግሎት ለመስጠት እንዲችል የዞኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጉራጊኛ ቋንቋ የሬድዮ የስርጭት አገልግሎት መስጠት መቻሉ በተለይም ለአርሶ አደሩ የመንግስት አቅጣጫ በቀጥታ ተደራሽ ለማድረግ አንዲሁም የጉራጊኛ ቋንቋን ለማልማት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ዋና አስተዳደሪው ገልፀዋል፡፡

የጉራጊኛ ቋንቋን አሁን ካለበት የመጥፋት አደጋ በማውጣት የስራ የትምህርት እና የሚዲያ ቋንቋ ለማድረግ የጀመርነው ጥረት ይበልጥ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል ዋና አስዳደሪው አቶ መሀመድ ጀማል፡፡

በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት የወልቂጤ ቅ/ጽ/ቤት በሰኔ 2001 ዓ.ም ሲቋቋም ጉራጊኛን ጨምሮ በሰባት ብሄረሰቦች የቋንቋ ስርጭ አገልግሎት ለመስጠት አላማን አድርጎ ነበር፡፡

ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች በጉራጊኛ ቋንቋ የስርጭት አገልግሎት መስጠት አለመቻሉን በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት የወልቂጤ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ንጋቱ ወልዴ ገልፀው በዚህ የተነሳ ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ በጉራጊኛ ቋንቋ ስርጭት አገልግሎት ላለመጀመር ዋና ምክንያት የነበረው የዞኑ ምክር ቤት የቋንቋውን ባህሪ ሊመጥን የሚችል ጥናት እስኪደረግ ድረስ በአማርኛ ቋንቋ መቀጠል እንዳለበት ያስተላለፈው ውሳኔ እንደነበር አቶ ንጋቱ ገልጸው ሆኖም ይህ ውሳኔ የህብረተሰቡን ጥያቄ ሊያስቆመው አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

የወልቂጤ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ይህንን ቀጣይነት የነበረው የህብረተሰቡን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ ላይ ለመምከር ጥረት ቢያደርግም በወቅቱ የነበረው አመራር የህብረተሰቡን ጥያቄ ከማስተጋባት ባለፈ የራሱ ጥያቄ አድርጎ ባለመንቀሳቀሱ ተግባራዊ ለማድረግ ሳይቻል ቀርቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለው የዞኑ መንግስት የህብረተሰቡን ስሜት በመጋራት የጉራጊኛ ቋንቋ የሚዲያ ቋንቋ እንዲሆን ጠንካራ አቋም በመያዝ የሰው ሀይልና ሌሎች የሚያስፈልጉ ድጋፎችን በማድረግ ስራውን ለመጀመመር ብርታት ሰጥቶናል ማለታቸው ከወልቂጤ ኤፍኤም ሬድዮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

ስለሆነም ተቋማችን በጉራጊኛ ቋንቋ የስርጭት አገልግሎት መጀመሩ የክልሉ መንግስትና የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ፍላጎትና እምነት መሆኑን በመገንዘብ በአሁኑ ወቅት አስፈላጊውን ዝግጅት ያጠናቀቅን በመሆኑ በያዝነው ሀምሌ ወር በጉራጊኛ ቋንቋ የሬዲዮ ስርጭት አገልግሎት መስጠት እንጀምራለን በማለት ዋና ስራአስኪያጁ አቶ ንጋቱ ወልዴ ተናግረዋል፡፡

በመረጃ ምንጭነት ገፃችን ምርጫዎ ስላደረጉ እናመሰግናለን!
= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *