ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት መረጃን መሰረት ያደረገ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰራ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታወቀ፡፡

ሀገር አቀፍ የሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት አራተኛ ዙር መረጃን መሰረት ያደረገ የህክምና አገልግሎት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተካሂዷል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ክልል የጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ በክልሉ የሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት በመሪነት ደረጃ ከተመረጡ አስራ አንድ ሆስፒታሎች አንዱ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጥ እንደ አዲስነቱ ሳይሆን ከነባር ሆስፒታሎች አገልግሎት አሰጣጥ የሚስተካከልበት ደረጃ መድረሱን ጠቁመው እስካሁን ከ120 ሺህ በላይ ዜጎች በሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ለዚህ ማሳያ መሆኑን የቢሮ ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በመንግስት የጤና ተቋማት ለህብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግሎቶች ቀልጣፋ ባለመሆናቸው ምክንያት ማህበረሰቡ በውድ ዋጋ እንኳን ቢሆንም ወደ ግል የህክምና ተቋማት ሄዶ መታከም ይመርጣል ያሉት አቶ ናፍቆት ብርሃኑ በቀጣይ ይህንን ለመቅረፍ በሆስፒታሎች የሚሰጠውን አገልግሎት ከወረቀት ንኪኪ ነጻ በማድረግና በማዘመን የህክምና አግልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸምሱ አማን በበኩላቸው የሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት አስፈላጊነቱ በህክምና ተቋማት የሚሰጡት አግልግሎቶች ሰውን ማዕከል ያደረጉ በመሆናቸው ጥራታቸውን ለማሻሻል የሚረዳ ነው፡፡

በመሆኑም በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙትን የሆስፒታሎች የአገልግሎት አሰጣጥ ለማቀራረብ የሚያስችላቸውን ልምድ የሚወስዱበትና በመደጋገፍ በመንግስት የሚመደበውን ውስን ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸው መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አብድራሂም በድሩ በበኩላቸው በሆስፒታሉ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት መረጃን መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

በሆስፒታሉ ዛሬ የተጀመረውን አራተኛው የሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት በሀገሪቱ ከሚገኙ አራት መቶ ስፒታሎች ውስጥ ተወዳድረው ለሽልማት የሚያበቃውን የመሪነት ደረጃ ማግኘቱን የገለጹት ስራ አስኪያጁ የአገናና የየም ልዩ ወረዳ የሳጃ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች በስሩ ይዞ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማሻሻል እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ከባለፉት ሁለት አመታት ተኩል ወዲህ በመጀመሪያ ሆስፒታል ደረጃ የሚሰጡትን አገልግሎቶች ለማህበረሰቡ ከመስጠት አንጻር የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገበ ቢሆንም በሪፈራል ደረጃ የሚሰጡትን አገልግሎቶች ከመስጠት አንጻር ውስንነት መኖሩን ገልጸዋል።

ለዚህም የግብዓትና የበጀት እጥረት ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር አብድራሂም እስካሁን የሚንቀሳቀሰው ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሆነ ከደቡብ ክልል ምንም ድጋፍ ሳያገኝ ከዩኒቨርስቲው በሚመደብለት በጀት ነው ብለዋል።

በጉራጌ ዞን የአገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ሀይሌ አራተኛ ዙር የሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ በመታደማቸው በሆስፒታላቸው የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሚያስችላቸውን ልምድ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

መጨረሻም የአራተኛ ዙር የሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት ለመተግበር የመግባቢያ ሰነድ የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ፣ የየም ልዩ ወረዳ የሳጃና የአገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች እንዲሁም የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በጋራ ፈርመዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *